
በጠፈር ምርምር ታሪክ የዓለማችን ሩቅ በራሪ የሆነው የናሳ ቮዬጀር 1 (Voyager 1) መንኮራኩር ከ49 ዓመታት በላይ ያለማቋረጥ ከተጓዘ በኋላ ከምድር አንድ የብርሃን ቀን (light-day) ርቀት ላይ በመድረስ ታሪክ ሰርቷል።
የብርሃን ቀን፣ ብርሃን በ24 ሰዓታት ውስጥ የሚጓዘው ርቀት ሲሆን፣ ወደ 25.9 ቢሊየን ኪሎ ሜትር ይሆናል። መንኮራኩሩ እዚህ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የደረሰው እ.ኤ.አ. ህዳር 9፣ ከቀኑ 7:16 ላይ ነው።
በካሊፎርኒያ በሚገኘው የናሳ ጄት ፕሮፐልሽን ላቦራቶሪ (JPL) የሚሰሩ የቮዬጀር ቡድን አባላት፣ የመንኮራኩሩ የሬዲዮ ሞገድ መልእክት በብርሃን ፍጥነት ተጉዞ ወደ ምድር ለመድረስ በወሰደው ጊዜ ልክ ከ24 ሰዓታት በኋላ ሐሙስ ላይ መልእክቱን ተቀብለዋል።
በዋሽንግተን የናሳ ዋና መሥሪያ ቤት የሄሊዮፊዚክስ ክፍል ዳይሬክተር ጆ ዌስትሌክ «አንድ የብርሃን ቀን መጓዝ ለአንድ መንኮራኩር እጅግ ከባድ ነው፤ ቮዬጀር ግን ከተጓዥነት የላቀ መንኮራኩር ነው። የቮዬጀር ተልዕኮ የፀሐይ ስርዓታችንን ውጨኛዎቹ ፕላኔቶች በመመርመር ለፕላኔታዊ ሳይንስ ባበረከተው አስተዋጽኦ ብቻ ስሙ በታሪክ የማይረሳ ሆኗል። አሁንም ድረስ ፀሐይን በተመለከተ ግንዛቤ በሚሰጡ የናሳ የሄሊዮፊዚክስ ተልዕኮዎች ውስጥ ማዕከላዊ ሆኖ ቀጥሏል» ብለዋል።
ሳይንቲስቶች የጠፈርን ግዙፍ ርቀቶች ለመለካት ብርሃንን ይጠቀማሉ። ብርሃን በባዶ ቦታ (vacuum) በሰከንድ 186,000 ማይል (299,000 ኪሎ ሜትር) ያህል ይጓዛል። የፀሐይ ብርሃን ወደ ምድር ለመድረስ 8 ደቂቃ፣ ወደ ኔፕቱን ለመድረስ ወደ አራት ሰዓት፣ ከዚያም ወደ ቮዬጀር 1 ለመድረስ ሌላ 20 ሰዓት ያህል ይወስዳል። ለማነጻጸር ያህል፣ አንድ የብርሃን ዓመት (light-year) 9.46 ትሪሊዮን ኪሎ ሜትር ነው።
የቮዬጀር ቡድን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከቮዬጀር 1 የሳይንስና የምርምር መረጃ ባይቀበልም፣ መንኮራኩሩ ያለማቋረጥ ወደ ምድር የሚያስተላልፈውን «የተሸካሚ ምልክት» (carrier signal) እየላከ ነው። የተልዕኮው መሐንዲሶች የብርሃን ቀኑን ምዕራፍ ለማረጋገጥ የተሸካሚ ምልክቱንና የጉዞ መስመር ስሌቶችን ተጠቅመዋል።
በከዋክብት መካከል ባለ ጠፈር (interstellar space) ውስጥ የሚገኙት ብቸኛ ሰው ሰራሽ የምርምር መሳሪያዎች የሆኑት ቮዬጀር 1 እና መንታው ቮዬጀር 2 የተወነጨፉት እ.ኤ.አ. በ1977 ነበር።
ሁለቱ መንኮራኩሮች ጁፒተርንና ሳተርንን የጎበኙ ሦስተኛና አራተኛ መንኮራኩሮች ሲሆኑ፣ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ምስሎች በመላክ የእነዚህን ዓለማትና የጨረቃዎቻቸውን ግንዛቤ የለወጡ የመጀመሪያዎቹ መንኮራኩሮች ናቸው። ቮዬጀር 2 ቀጥሎ ኔፕቱንና ዩራነስን መርምሯል። ሁለቱም መንኮራኩሮች በሰፊ ርቀት ላይ የፀሐይን መግነጢሳዊ መስክ ለውጦች መለካታቸውን ቀጥለዋል።
የናሳው ጀት ፕሮፐልሽን ላብራቶሪ ዳይሬክተር ዴቭ ጋላገር «ቮዬጀር 1 የብርሃን ቀን ጣሪያን ማቋረጡ ልዩ በሆነ የግኝት ጉዞ ላይ ሌላ ታሪካዊ ገድል ነው። ከሁሉም በላይ ይህ ምዕራፍ እነዚህን መንኮራኩሮች ለገነቡ፣ ፕሮግራም ላደረጉና ዛሬ በረራውን ለሚከታተሉ እንዲሁም ከምድር ጋር ተገናኝተው እንዲቆዩ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ተግዳሮቶች ላሸነፉ ቡድኖች ምስክር ነው» ብለዋል።
ቮዬጀር 1 እና 2 ከሳይንሳዊ መሣሪያዎቻቸው ስብስብ በተጨማሪ፣ አንድ ቀን ሊያገኛቸው ለሚችል ማንኛውም ስልጣኔ ከምድር የተላከ መልእክት እንዲሆን ከምድር የተሰበሰቡ ምስሎችንና ድምፆችን የያዘ፣ በወርቅ የተለበጠ የመዳብ ፎኖግራፍ የሆነውን «ወርቃማ ሪከርድ» (Golden Record) ይዘዋል።
የካልቴክ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሬይ ጃያዋርዳና «ምድርን ከለቀቀ ወደ ግማሽ ምዕተ ዓመት ገደማ በኋላም፣ የቮዬጀር ተልዕኮ የሰው ልጅ ምርምር ድንበሮችን መግፋቱን ቀጥሏል። ይህ ታላቅ ጉዞ ለአሥርት ዓመታት ተልዕኮውን የመሩትን የካልቴክ የፊዚክስ ሊቅና የJPL ዳይሬክተር ኤድ ስቶንን ራዕይ፣ እንዲሁም ያንን ራዕይ ወደ ፊት ያስተላለፉ ተመራማሪዎችና መሐንዲሶች የምርምር ጉጉትና ጽናት ያንጸባርቃል። ለሳይንስ ከሰጠው እጅግ ሰፊ አስተዋጽኦ ባሻገር፣ ቮዬጀር ስለ ሰው ልጅ መንፈስ ጥልቅ የሆነ ነገርም ያሳያል። ጉዞው በመጨረሻ ወዴት እንደሚያደርሰው ፈጽሞ ላናውቅ እንችላለን፤ ነገር ግን መጓዙን ይቀጥላል፤ ይህም የሰው ልጅ እዚህ እንደነበረና ህዋውን ለመመርመር የሄደበትን ርቀት የሚያረጋግጥ ዘላቂ ምስክር ነው» ብለዋል።
በ- ዳንኤል መኮንን









