December 2, 2025
የሰውነትን የበሽታ መከላከያ ሃይል፣ በተለይ ነጭ የደም ሴል በማጥቃት በቀላሉ ሰውነት ለበሽታ የሚያጋልጠው የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ የበርካቶችን ህይወት እየነጠቀ ይገኛል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ 40 ነጥብ 8 ሚሊዮን አዋቂዎች እና 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሕጻናት በደማቸው ውስጥ ኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ እንደሚገኝባቸው በ2024 የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

በሀገራችን የኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታን የመከላከል እና የመቆጣጠር ሥራዎችን የማጠናከር ተግባር እየተከናወነ ያለ ሲሆን፣ በየግዜውም የግንዛቤ ማስጨበጨ መድረክ ይከናወናል፡፡ በሀገራች በየዓመቱ እየታወሰ የሚከበረው የዓለም የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀን በበርካታ ሁነቶች ታስቦ የዋለም ነበር፡፡
የኤድስ ሂልዝ ኬር ፋውንዴሽን ከጤና ሚኒስቴር እንዲሁም ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመሆን እለቱን ያከበረ ሲሆን የኤች አይ ቪ ኤድስ ከሥር መሠረቱ መፍታት እና እመርታዊ ለውጥ ለማምጣት እንደሚያሻም አመላክቷል፡፡ በኅብረተሰቡ ውስጥ ለቫይረሱ መስፋፋት የሚሰጠው ግምት እያነሰ መምጣት በተለይም አፍላ ወጣቶች እና ወጣት ሴቶች አሉታዊ የአቻ ግፊትን አለመቋቋም፤ ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት መኖር እና ሌሎች ተጓዳኝ ችግሮች ለቫይረሱ ተጋላጭነት ቀዳሚ ጉዳይ መኾናቸውንም በመድረኩ ተነስቷል፡፡

ቫይረሱን በመከላከል እና በመቆጣጠር ረገድ እየተሠሩ ያሉ ተግባራት መሻሻል የሚታይባቸው ቢሆን ባንድም በሌላም ዓለም አቀፍ ተቋማት በየሀገራቱ የሚያደርጉት ድጋፍ ላይ በገጠመ ችግር ቫይረሱ በደማቸው ላለባቸው ሰዎች ተገዳሮት እንደሆነም ከተነሱ ጉዳዩች ማሀል አንዱ ነው፡፡
ኤች አይ ቪ ኤድስ፣ አምራች ዜጎችን የሚጎዳ በመሆኑ በኢንዱስትሪዎች እና በትምህርት ተቋማት ላይ ለወጣቶች እና ሴቶች ግንዛቤን ማሳደግ ላይ መስራት እንዳለበት ብሎ የቫይረሱ ስርጭት ቀድሞ ከነበረበት የቀነሰ ቢኾንም በህብረተሰቡ ዘንድ አሁንም ከፍተኛ መዘናጋት እንዳለ መስተዋሉም ተነግሯል፡፡

የኤች አይ ኤድስ ቀን ”ተግዳሮቶችን በመቋቋም የኤች አይ ቪ ኤድስ ምላሽን በዘላቂነት እናረጋግጥ” በሚል መሪ ቃልም ተከብሯል፡፡












