NBC Ethiopia
November 30, 2025
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከደብረ ኤሊያስ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ሲሆን ባስተላለፉት መልእክትም፣ አካባቢው የሚታወቀው በሰላም ወዳድነቱ እና በአምራችነቱ ነው ብለዋል። ለሃይማኖት እና ለዘመናዊ ትምህርት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ መኾኑንም ተናግረዋል።

ለሀገር አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሊቃውንት የፈለቁበት፣ ለሀገር የሚበቃ ምርት የሚቀርብበት አካባቢ መኾኑንም ገልጸዋል። ይህ ሰላም ወዳድ እና አምራች ማኅበረሰብ አሁን ላይ ግን በጸጥታ ችግር ብዙ ዋጋ ከፍሏል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በደብረ ኤሊያስ የደረሰው የጸጥታ መታወ የከፋ እንደነበርም አስታውሰዋል።
አውዳሚ የኾነ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት እንደደረሰም በመግለፅ፣ ንጹሃን በስቃይ እና በጭንካኔ የተገደሉበት መሆኑን ነው የተናገሩት።

አካባቢ ለልማት ትልቅ አቅም ያለው ቢኾንም በጸጥታ ችግር ምክንያት ማልማት ሳይችል ቆይቷል። የደብረ ኤሊያስ አርሶ አደሮች እንዳያመርቱ፣ ምርታቸውን ለገበያ እንዳያቀርቡ እንግልት ሲደረግባቸው እንደቆየም ተናግረዋል።
የትምህርት እና የጤና ተቋማት ተዘግተው መቆየታቸው፣ ማኅበረሰቡን የሚያዋርድ ተግባር መፈጸሙንም አንስተው፣ ከዚህ በላይ የሚደርስ ግፍ የለም በናለት ድርጊቱን ኮንነዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ አክለው ወጣቶች እና መላው ማኅበረሰብ ለሰላም በአንድነት መነሳት እንደሚጠበቅበት፣ ሰላም ወዳዱ እና ትርፍ አምራቹ አካባቢ ሲታወክ ዝም ብሎ ማየት እንደማይገባ አስገንዝበዋል ተናግረዋል።
የአካባቢውን ሰላም አስተማማኝ ለማደረግ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ከክልሉ የጸጥታ ኃይል ጋር በአንድነት እንዲሠሩም አስገንዝበዋል።
በውይይቱ ከርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተጨማሪ ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን ( ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ በበከኡላቸው፣ ሕዝባችንን አንገት ያስደፋ ችግር ገጥሞን ቆይቷል ። ነገር ግን በተሠራው ሥራ አሁን ላይ በእጅጉ እየተሻሻለ የመጣ ሰላም ታይቷል ያሉት አሥተዳዳሪው ይሁን እንጂ አሁንም ማስተካከል የሚገባን ብዙ ጉዳይ አለ ነው ያሉት።

የደብረ ኤሊያስ ወረዳ ሕዝብ በከፍተኛ ችግር ውስጥ መቆየቱን ተናግረዋል። ወረዳው ከራሱ በላይ ለሌሎች የሚያተርፍ ቢሆንም፤ በራሱ ልጆች እንዳያመርት፣ ልጆቹ እንዳይማሩ ተደርጎ ቆይቷል ብለዋል።
ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዲሆኑ፣ መምህራን እንዳያስተምሩ ኾነው መቆየታቸውን ተናግረዋል። በደብረ ኤሊያስ ወረዳ ከአማራ ሕዝብ ባሕልና እሴት ያፈነገጠ ድርጊት ሲፈጸም መቆየቱንም ገልጸዋል።
የአካባቢው ሕዝብ በራሱ ልጆች ሲሰቃይ መክረሙን እንዲሁም፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች እንዳይመክሩ፣ እንዳያስታርቁ በጽንፈኛ ቡድኑ ሲሰቃዩ መኖራቸውንም ተናግረዋል። የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ማስፈን እንደሚገባም ገልጸዋል።

በዞኑ በርካታ ችግሮች ተፈጥረው ቢቆዩም አሁን ላይ ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሠራ መኾኑን አስገንዝበዋል። የሀገር መከለካያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኃይል ባደረጉት ተጋድሎ የተሻለ ሰላም መፈጠሩን በመጥቀስ የፀጥታ አካላትን አመስግነዋል።
አስተማማኝ ሰላም እንዲፈጠር የአካባቢው ማኅበረሰብ አሁንም የታጠቁ ኃይሎች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ ግፊት እንዲያደርግ የጠየቁት አስተዳዳሪው፣ የሰላም አማራጭ ክፍት ነው፤ የሰላም አማራጭን የሚቀበሉትን እንቀበላለን፣ የሰላም አማራጭን በሚገፉት ላይ የሕግ ማስከበር ርምጃው ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።












