NBC Ethiopia
November 29, 2025′
አማራ ባንክ አ.ማ የባለአክሲዮኖች 4ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ አካሂዷል። በጠቅላላ ጉባኤው ባንኩ የ2017 በጀት ዓመት አጠቃላይ አፈፃፀሙን ለባለአክሲዮኖች አቅርቧል።
በጉባኤው ባንኩ በበጀት ዓመቱ የቀረቡለትን ዕድሎች በመጠቀም ተልዕኮውን መወጣት እንደቻለ ተነስቷል፡፡ ባንኩ 2016 እና በ2017 መጀመሪያ ሩብ አመት ገብቶበት ከነበረው ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮት በመውጣት ከፍተኛ ስኬት ማስመዝገብ መቻሉ ተገልጿል።

ቀደም ሲል ባንኩ ባጋጠሙት ውስብስብ ተግዳሮቶች ለኪሳራ ተዳርጎ ነበር ያሉት የአማራ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዮሃንስ አያሌው (ዶ/ር) በተወሰዱ የሪፎርም ማሻሻያዎች ከኪሳራ ማንሰራራት መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
የአማራ ባንክ ጠቅላላ ሀብት 43 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፤ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ 23.2 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ነው ዋና ስራ አስፈፃሚው የተናገሩት፡፡ እንዲሁም ባንኩ በበጀት ዓመቱ ከታክስ በፊት 655 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገቡ ተመላክቷል፡፡ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ85 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ እንዳለው ተገልጿል፡፡
ባንኩ በ2017 በጀት ዓመት አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን በ26 በመቶ በማሳደግ ወደ 31.5 ቢሊዮን ብር ማደጉ ሲገለጽ ፤የባንኩ አጠቃላይ ገቢ በ29 በመቶ በማሳደግ ወደ 5.6 ቢሊዮን ብር መጨመር መቻሉንም ነው ዋና ሥራ አስፈፃሚው ለጠቅላላ ጉባኤው ተሳታፊዎች ይፋ ያደረጉት፡፡
ባንኩን ወደ ዘላቂ እድገትና ልቀት ለማሸጋገር ከፊቱ የሚያጋጥሙትን ውስብስብ አለም ዓቀፍና ሀገራዊ ኢኮኖሚ ጫናዎችን ለመቋቋም ጠንካራ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫ በመስጠት እየተሰራ መሆኑ በባንኩ አራተኛ ዓመታዊ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ተመላክቷል፡፡
በ – ሰላማዊት ወልደገሪማ












