በተመልካች ድርቅ እየተመታ ያለው የክለቦች ዓለም ዋንጫ ወደ መቋጫው ላይ ታላላቅ የአውሮፓ ቡድኖች ሲገናኙበት ትኩረት መሳብ ጀምሯል። ትላንት በግማሽ ፍጻሜው የብራዚሉን ፍሉሚኔንሴን ያሸነፈው ቼልሲ ለዋንጫው የሚቀናቀነውን ባላጋራ ዛሬ የሚያውቅ ይሆናል።
በብዙዎች አስቀድሞ የዋንጫ አሸነፊነት ቅድሚያ ግምት የተሰጣቸው ሪያል ማድሪድ እና ፒኤስጂ ምሽት 4 ሰዓት የሚያደርጉት ፍልሚያ ከፍጻሜ በፊት የሚደረግ ሌላ ፍጻሜ በሚል በእጅጉ ተጠባቂ ሆኗል።
የዓለም የክለቦች ዋንጫ የሚለውን በአዲስ የውድድር ስርዓት እንዲካሄድ ካነሳሱ ሰዎች ውስጥ ዋናኞቹ የሪያል ማድሪድ እና ፒኢስጂ ባለስልጣናት ሲሆኑ፣ ከዚህ የጋራ አላማ በስተቀር ግን ሁለቱ ቡድኖች እንደ ባላንጣ የሚተያዩና የሚጠላሉ ለመሆናቸው ባለፉት ዓመታት የነበራቸው ግንኙነት ያሳያል።
በፋይናንስ ጡንቻቸው ተጫዋች በመነጣጠቅ፣ በክለብ ሃላፊዎቻቸው የሃይለ ቃል ልውውጥ በማድረግ በማሃላቸው ያለው ቁርሾ ተባብሶ ይገኛል። በተለይም በምሽቱ ጨዋታ በሎስ ብላንኮዎቹ በኩል የቀድሞ ከለቡን የሚገጥመው ኪሊያን ምባፔ በሁለቱ ክለቦች መካከል ለቆየው ጸብ ዋነኛ አቀጣጣይ ሆኗል።
በፒኤስጂ ያለውን ውል አጠናቆ በነጻ ዝውውር ማድሪድን የተቀላቀለው ምባፔ በምሽቱ ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀድሞ ቡድኑን የሚገጥም ሲሆን፣ ዐብይ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ሆኖ እየተዘገበ ይገኛል። ፈረንሳዊው ኮከብ ከፓሪሱ ቡድን የለቀቀበት ዋነኛ ምክንያት የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ለማሳካት የነበረ ቢሆንም ክለቡን በለቀቀ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ፒኤስጂ ባለ ትልልቅ ጆሮውን ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ አሳክቷል።
የሪያል ማድሪዱ ፕሬዚዳንት ፍሎረንቲኖ ፔሬዝ ለክለቦች ዓለም ዋንጫ እንደ አዲስ መጀመር ከማንም በፊት ቀድመው የተሟገቱ ሲሆን፣ ተጫዋቾቻቸው ለቻምፒዮንስ ሊግ የሚሰጡትን ትኩረት በሚመጣጠን መልኩ ለክለቦች ዓለም ዋንጫም ጉጉት እንዲያሳዩ አሳስበዋል። ከጉዳት ጋር በተያያዘ አስጊ ስጋት የሌለባቸው ሎስ ብላንኮዎቹ፣ አዲሱ ተከላካያቸው ዲን ሃውሰንን በቅጣት ምክንያት በምሽቱ ጨዋታ አያገኙትም።
በአሰልጣኝ ዣቪ አሎንሶ የመሰለፍ እድል እየተሰጠው ያለው ወጣቱ አጥቂ ጎንዛሎ ጋርሺያ በመጀመሪያ አሰላለፍ ሊካተት እንደሚችል እየተዘገበ ይገኛል። የወቅቱ የቻምፒዮንስ ሊግ ባለ ድል ፒኤስጂ በወጣት የቡድን ስብስቡ እየታገዘ የመድረኩ አሸናፊ ሊሆን እንደሚችል ቅድመ ግምት የተሰጠው ቡድን ነው።
በልዊስ ኤንሪኬ የሚሰለጥነው የፈንሳዩ ቡድን የሶስትዮሽ ድል ባለቤት በመሆን አስደናቂ የውድድር ዓመት አሳልፏል። እንደ ብራድሊ ባርኮላ፣ ኦስማን ዴምቤሌ እና ክቪቻህ ክቫራትስኬሊያ ያሉ ኮከቦች በጥሎ ማለፉ ባየር ሙኒክን ባሸነፉበት ጨዋታም አሁንም የቡድኑ አስፈሪ ጥምረት መሆናቸውን በድጋሚ አስመስክረዋል።
በጥቅል የ125 ሚሊዮን ዶላር አሸናፊ የሚያደርገውን ዋንጫ ለማሸነፍ የበረታ ፉክክር የሚታይበት፣ ከወትሮው በተሻለም የተመልካች ትኩረት የሚያገኝ ጨዋታ እንደሚሆን ይጠበቃል። ተጠባቂው ጨዋታ ምሽት 4 ሰዓት በኒው ጄርሲ ሜት ላይፍ ስታዲየም ይጀመራል።
በ-አልፈሪድ ነስሮ












