የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት የ90 ቀናት የንቅናቄ ስራዎች ያሉበትን ደረጃ በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎችን ሰጥተዋል።
ከ15 ቀናት በፊት ከመላው አመራር ጋር በመወያየት ዝርዝር አቅጣጫ የተሰጠባቸው 18ቱም ከተማ አቀፍ የክረምት ንቅናቄ አጀንዳዎች ዙሪያ አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ከንቲባዋ ገልጸዋል።
ውጤታማ ስራ ከታየባቸው መካከል በገበያ ማረጋጋት፣ ስራ ዕድል ፈጠራ፣ ከተማ ግብርናና ሌማት ትሩፋት፣ ገቢ አሰባሰብ፣ የክረምት በጎ ፍቃድ ስራዎች፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር፣ የሁለተኛ ዙር ኮሪደር ልማት ቀሪ ስራዎችን ቆጥሮ ማጠናቀቅ እና ሌሎች ትላልቅ ፕሮጄክቶች አፈጻጸም ዙሪያ አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆናቸውን በተደረገው ግምገማ ተረጋግጧል ነው ያሉት።
የህብረተሰቡን የኑሮ ጫናዎችን ለማቃለል በተሰራው የተቀናጀ ስራ የከተማዋ የገበያ ማዕከላት፣ የእሁድ ገበያዎች፣ የከተማ ግብርናና የሌማት ትሩፋት ስራዎች፣ አምራች ኢንዱስትሪዎች እና መሰል ዘርፎች የምርት አቅርቦት ሰንሰለትን በማሳለጥ ከፍተኛ አበርክቶ እንዲኖራቸው መደረጉም በግምገማው ተነስቷል።
ቀሪ ስራዎችን በተሟላ መልኩ ለማሳካት በየደረጃው ያለው አመራር ለላቀ ውጤት በትብብር እንዲረባረብ አቅጣጫ መሰጠቱን የከንቲባ ጽ/ቤት ያደረሰን መረጃ ያመለክታል።












