
ለወራት ወደ አርሰናል ለመጓዝ ተስማምቷል ሲባል የቆየው ዙቢሜንዲ በስተመጨረሻ ወደ እንግሊዝ የሚያደርገው ዝውውር መቋጫ ማግኘቱን ዘ አትሌቲክ ዘግቧል።
ተጫዋቹ በለንደን የአርሰናል ሀላፊዎችን በማግኘት ንግግር እንደሚያደርግ እና አስፈላጊ የዝውውር ሂደቶችን እንደሚያጠናቅቅ ታውቋል። መድፈኞቹ በሪያል ሶሲዳድ የተጠየቀውን የ60 ሚሊዮን ፓውንድ የውል ማፍረሻ ለመክፈል ፈቃደኛ መሆናቸው እና ከተጫዋቹም ጋር በግል ጥቅማጥቅም ዙሪያ መግባባት ላይ መድረሳቸው አይዘነጋም።
አርሰናል በያዝነው የክረምት ገበያ በአማካኝ ክፍል ጆርጊኒዮን እና ቶማስ ፓርቴን ማጣቱን ተከትሎ ተተኪ ተጫዋቾችን የማስፈረም ግዴታ ውስጥ ገብቷል። አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ዙቢሜንዲን ለአመታት ሲከታተለው እንደቆየ እና የተጫዋቹ አድናቂ መሆኑ ይነገራል።
ተጫዋቹ የተጋጣሚ ቡድንን ማጥቃት በማጨናገፍ እና መስመር ሰንጣቂ ኳሶችን በማቀበል ስኬታማ እንደሆነ ለአመታት አሳይቷል። የ26 አመቱ ስፔናዊ በተጠናቀቀው የስፔን ላሊጋ በ36 ጨዋታዎች ተሰልፎ 4 የጎል ተሳትፎ ማድረግ ችሏል።
በ-አልፈሪድ ነስሮ












