
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (INSA) ከ6 ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን የ5ኛ ዙር የሳይበር ታለንት ሰመር ካምፕ ቻሌንጅ ስልጠና ያጠናቀቁ 1140 ሰልጣኞችን በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
ከነሐሴ 5/2018 ዓ/ም ጀምሮ ሲሰጥ የነበረው ይህ ሰመር ካምፕ ከደኅንነት እና ቴክኖሎጂ ስልጠናዎች ጎን ለጎን የሰልጣኞችን አጠቃላይ ጤንነት እና ሥነ-ልቦናዊ ጥንካሬ የሚያጎለብቱ ስልጠናዎች ጨምሮ ሌሎች የፈጠራ እና የማሰላሰል ክህሎት ማሳደጊያ ስልጠናዎችን እንደወሰዱም ተመላክቷል፡፡
ተመራቂዎቹ በአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ፣ ባሕር ዳር፣ ሐረማያ፣ ጅማ፣ ደብረ ብርሃን እና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም በኢመደአ የታለንት ማዕከል ሲሰለጥኑ የቆዩ መሆናቸው ተጠቁሟል።
በምረቃው ላይ ንግግር ያደረጉት የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ፣ ሀገራዊ የድጅታል ቴክኖሎጂ የሚረጋገጠው ዘመናዊ ቴክኖጂ በመግዛት እና በመጠቀም ሳይሆን በራስ አቅም የቴክኖሎጂ ባለቤት በመሆን ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በቂ የሳይበር ደህንነት ባለሙያ እጥረት እንዳላት የገለጽት ዋና ዳይረክተሯ ይህን ችግር ለመቅረፍ እያንዳንዱ ተቋም የራሱ የሳይበር ደህንነት ባለሙያ ማፍራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የመዝግያ ንግግር ያደረጉት የትምህርት ሚኒስትር ፕ/ር ብረሃኑ ነጋ ብቁ የሀገሪቱ የሳይበር ደህንነት ባለሙያዎችን ለመፍራት የሚደረገው ጉዞ አካል የሆነው የኢንሳ 5ኛ ዙር የሳይበር ታለንት ሰመር ካምፕ ስልጠና የዚህ ተጨባጭ ራዕይ ማሳያ ነው ብለዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ባለፉት 5 አመታት 2304 የሳይበር ደህንነት ሰልጣኞችን በማስመረቅ የሳይበር ደህንነትን የማስጠበቅ እና የዘርፉን ባሉሙያዎች ፍልሰት በማስቀረት የ2030 ድጅታል ኢትዮጵያ ጉዞ እውን ለማድረግ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑ ተገልጿል።
በአብርሃም ኃይሉ








