ኢትዮጵያ የማርበርግ በሽታ ወረርሽኝን በአጭር ጊዜ የተቆጣጠረችበት መንገድ ለአፍሪካ አህጉርና ለሌሎች ሀገራት አርዓያ የሚሆን ተግባር መሆኑን በ5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ (CPHIA 2026) የተሳተፉ ባለሙያዎች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የከፈቱት 5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ “የአፍሪካ የጤና ደኅንነት እና ሉዓላዊነት፤ ከጤና ጥገኝነትና ተጋላጭነት ወደ ባለቤትነት እና ጽናት የሚደረግ ሽግግር” በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ይገኛል።
በጉባኤው ላይ የተሳተፉት ስፔናዊቷ የጉባኤው ተሳታፊ ዶክተር ማሪያ ኔይራ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ የማርበርግ ወረርሽኝን የተቆጣጠረችበት መንገድ ግልጽነት የተላበሰና በሌሎች ሀገራትም ሊተገበር የሚገባው ምርጥ ተሞክሮ ነው።
በተለይም ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በቅርበት የተከናወነው የመረጃ ልውውጥ፣ ፈጣን ምላሽ አሰጣጥና ወረርሽኙን በቶሎ የመቆጣጠር አቅም ከፍተኛ አድናቆት የሚገባው መሆኑን አስገንዝበዋል።
ከናሚቢያ ዩኒቨርሲቲ የመጣችው ክሌዱላ ጃኮብ በበኩሏ፣ ወረርሽኝን በሦስት ወራት ውስጥ መቆጣጠር መቻል ትልቅ ስኬት መሆኑን ጠቅሳለች።
አፍሪካውያን በጋራ በመሰባሰብ ከእርስ በርስ መማማር ባለፈ የተገኙ ልምዶችን በተግባር ማዋል እንደሚገባቸው ተናግራለች።
ሌላኛዋ የናሚቢያ የጤና ሚኒስቴር ተሳታፊ ሞኒካ ዴንሲ እንዳለችውም፣ አፍሪካውያን ከኢትዮጵያ ሊወስዱት የሚገባው ቁልፍ ተሞክሮ ወረርሽኝን ቀድሞ በመለየትና ንክኪ ያላቸውን ሰዎች በመከታተል በሽታው ሳይዛመት መቆጣጠር ነው።
ለዚህም አህጉሪቱ ሁልጊዜ በጋራና በቅንጅት መሥራት እንዳለባት ጠቁማለች።
በአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) እና በኢትዮጵያ መንግሥት ትብብር በተዘጋጀው በዚህ ጉባኤ ላይ ከ100 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ከ30 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ታድመዋል።














