በኢትዮጵያ የዘመናዊ ግብርና አሰራር መስፋፋት ለሀገራዊ ምርታማነትና ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት መሰረት እየሆነ መምጣቱን የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

በግብርና ዘርፍ በመስፋፋት ላይ ያሉ ዘመናዊ የአመራረት ዘዴዎችና የልማት እንቅስቃሴዎች የምርት አቅምን ከማሳደግ ባለፈ የሀገር ውስጥ የምግብ ፍላጎትን ለመሸፈን፣ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘትና ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር አዳዲስ አማራጮችን እየከፈቱ መሆኑንም ምሁራኑ አመልክተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የግብርናና እንስሳት ሕክምና ኮሌጅ የእንስሳት ሥነ-ምግብ መምህርና ተመራማሪ ዋሲሁን ሀሰን (ዶ/ር) እንደገለጹት በግብርናው ዘርፍ እየታየ ያለው ለውጥ የአመራረት ሥርዓቱን ከባህላዊ አሠራር ወደ ቴክኖሎጂ መር አሠራር እያሸጋገረው ነው።

በተለይም የመስኖ ልማት መስፋፋት አርሶ አደሮች በዝናብ ወቅት ብቻ ሳይገደቡ በተለያዩ ጊዜያትም ምርት እንዲያመርቱ ዕድል እየፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል።
የግብርና ማሽነሪዎች አጠቃቀም መጨመርም የአመራረት ሂደቱን በማቀላጠፍ ጊዜንና የሰው ጉልበትን በተሻለ ሁኔታ ለመጠቀም እያገዘ መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህ አንጻር በበጋ መስኖ የሚመረተው ስንዴ መስፋፋት የሀገሪቱን የስንዴ አቅርቦት ከማጠናከር ባለፈ ምርቱን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል አቅም መፍጠሩን አመልክተዋል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ግብርናና እንስሳት ሕክምና ኮሌጅ ዲንና የአፈር ልማት፣ የሰብል እንክብካቤና ንጥረ ነገር ባለሙያ ሰለሞን ቱሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ግብርና በቤተሰብ ደረጃ የሚከናወኑ የምርት ሥራዎችን ጨምሮ ለምግብ ፍጆታና ለገቢ ማስገኛ ያለው ሚና እየጎላ መምጣቱን ገልጸዋል።

ለአርሶ አደሩ እየተደረገ ያለው ሞያዊ እገዛም በየጊዜው እየተሻሻለ መምጣቱን እና ይህም ከምርት ዕድገት በተጨማሪ ብክነትን ቀንሶ በጥራት ለማምረት እየተሰራ ያለውን ስራ ውጤታማ እያደረገው ነው።
በተጨማሪም የጓሮ አትክልት ልማት፣ የዶሮ እርባታና የንብ ማነብ ሥራዎች በሌማት ትሩፋት እንቅስቃሴ የተስፋፉ የምርት ዘርፎች በመሆናቸው በገጠርና በከተማ የሚኖሩ ዜጎች በግብርና ሥራዎች በቀጥታ እንዲሳተፉ ዕድል መፍጠራቸውን አስረድተዋል።

በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የሚታየው መስፋፋትም ለሀገሪቱ የወጪ ንግድ አዲስ አቅም እየፈጠረ መሆኑን ሰለሞን (ዶ/ር) ጠቅሰዋል።
እንዲሁም የቡና ምርቶት ለውጭ ገበያ መቅረብ የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ ትልቅ ድርሻ እየተወጣ መሆኑን አመልክተዋል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ምጣኔ ባለሙያና ተመራማሪ አደባ ገመቹ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በስንዴና በሩዝ ምርት ላይ እየተመዘገቡ ያሉ መሻሻሎች ሀገሪቱ በምግብ አቅርቦት ከውጭ ያላትን ጥገኝነት ለመቀነስ የሚያስችል አቅም እንደሚፈጥር አስረድተዋል።

የሀገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ የውጭ ምርት ግዢን በመተካት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ለመቆጠብ ከማገዙም በላይ በምርት ሂደቱ ዙሪያ የተለያዩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን እንደሚያነቃቃ ገልጸዋል።
በተለይም የግብርና ምርቶችን ማቀነባበር፣ ማከማቸት፣ ማጓጓዝና ለገበያ ማቅረብ የሚያካትተው የእሴት ሰንሰለት ለወጣቶችና ለሌሎች ዜጎች ተጨማሪ የሥራ ዕድሎችን እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችና የምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች መስፋፋት ጥሬ ዕቃዎችን ወደ ተጨማሪ እሴት ወዳላቸው ምርቶች ለመቀየር፣ ለአምራቾች የገበያ አማራጭ ለመፍጠርና የሀገር ውስጥ ምርትን ተወዳዳሪ ለማድረግ ወሳኝ መሠረት መሆናቸውንም አብራርተዋል።
ይሁንና የተጀመሩትን ለውጦች ወደ ዘላቂ ውጤት ለማሸጋገር የምርት ጥራትን፣ የአቅርቦት ቀጣይነትንና የማቀነባበር አቅምን በተቀናጀ መንገድ ማጠናከር እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል።
ምንጭ- ኢዜአ









