በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ጉልህ አሻራ ያላቸው ዶክተር ነገደ ጎበዜ፣ ጥቅምት 6 ቀን 1936 ዓ.ም. በደሴ ከተማ ተወለዱ።

ለኢትዮጵያ ትምህርት መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካበረከቱትና የትምህርት ዳይሬክተር በመሆን ካገለገሉት አባታቸው አቶ ጎበዜ ጣፈጠ እና ከእናታቸው ወይዘሮ በላይነሽ እጅጉ ተወልደዋል።
የ13 አመቱ ነገደ፣ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የአሜሪካ ጉዟቸውን አጠናቀው ወደ አዲስ አበባ በተመለሱበት ጊዜ ለጃንሆይ «እንኳን ደህና መጡ» የሚል ግጥም ጽፈው ነበር።
የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በደሴ ወይዘሮ ስኂን እና በአዲስ አበባ ጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤቶች ተከታትለዋል።
ዶክተር ነገደ፣ በወቅቱ “የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ” ተብሎ ይጠራ በነበረው የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
ከፍተኛ ትምህርታቸውን ለመቀጠል ወደ ፈረንሳይ በማቅናት በኤክስ አን ፕሮቨንስ (Aix-en-Provence) ዩኒቨርሲቲ በ1967 ዓ.ም. በሕግ የፒኤችዲ (PHD) ዲግሪያቸውን የተቀበሉ
ሲሆን፣ ወደ ፖለቲካው ዓለም ለመግባት መንገድ የሆናቸው ትምህርታቸዉን በሚከታተሉበት ወቅት ከፈረንሳውያን ጓደኞች ጋር የማርክሲዝም ሐሳቦችን በመጋራታቸው ነበር።

በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር ውስጥ በንቃት በመሳተፍ እስከ ፕሬዝዳንትነት የደረሱ ሲሆን፣ በወቅቱ በአውሮፓ አልፎም በአለም አቀፍ ደረጃ በነበሩ የወጣቶች ንቅናቄ ተጽዕኖ፣ የተማሪዎችን ማህበር የፖለቲካ አቋም ወደ ስር ነቀል ለውጥ እንዲያመራ አድርገዋል።
አላማውን፣ ለሀገር ልማት ገንቢ ሀሳቦችን ለንጉሰ ነገስቱ በመሰንዘር፣ እድገትን ለማፋጠን የሚረዱ ገንቢ በውይይት ለመዘየድ የተቋቋመውን “በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር” የተሰኘውን ማህበር ተቀላቀሉ። በዚያም የትምህርት ወጪያቸው በኢትዮጵያ የትምህርት ሚኒስትር ይሸፋን ነበር።
ነገር ግን በ1956 ቬና በነበረው ውይይት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር የማርክሲዝምን ሀሳቦች ርዕዮተ-ዓለም በመደገፍ የንጉሰ-ነገስቱን አገዛዝ በመቃወም ከንጉሱ ጋር ተቆራረጡ።
በ1960 ዓ.ም. የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) መሥራች አባል ሆኑ። የንጉሠ ነገሥቱን አገዛዝና ፊውዳሊዝም በመቃወም ንቅናቄ ውስጥም ገብተው ነበር። ይህ ትግል ንጉሡን ከሥልጣን ያወረደውን የ1966 ዓ.ም. አብዮት መንገድ ከጠረጉ እንቅስቃሴዎች አንዱ ነበር። ዶክተር ነገደ ይህንን አብዮት መሠረት በማድረግ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ነበር።

በወቅቱ ከነበረው የደርግ ገዢ ጋር በፈጠሩት በመኢሶን እና የደርግ የትብብር ዘመን የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤት አባል እና የ«አብዮታዊት ኢትዮጵያ» መጽሔት ዋና አዘጋጅ ሆነው ሠርተዋል።
ይሁን እንጂ በዲሞክራሲያዊ መብቶች አዋጅ ረቂቅ ዙሪያ በተፈጠረ ልዩነት መኢሶን ደርግን መደገፉን አቋርጦ ወደ ተቃውሞ ገባ። በዚህ ጊዜም በርካታ የመኢሶን አባላቶች ሲታሰሩ እና ሲገደሉ እሳቸው በወቅቱ ለሥራ ጉዳይ ወደ አውሮፓ አቅንተው ስለነበር ከእስርና ከግድያ መትረፍ ችለዋል።
በፈረንሳይ ስደት ውስጥ ሆነውም ዶክተር ነገደ ትግላቸውን አላቋረጡም፤ ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ሰብአዊ መብት እና ዲሞክራሲያዊ ሽግግር የሚታገሉ የተለያዩ ድርጅቶችን፣ ዓለም አቀፍ የእርቅ ኮንፈረንሶችን እንዲሁም ነጻ የራዲዮ ጣቢያዎችን በማቋቋም ከፍተኛ ትግል አድርገዋል።
በሥነ ጽሑፍ እና በምሁራዊ ንግግሮቻቸው በስፋት የሚታወቁት ፖለቲከኛው ዶክተር ነገደ ጎበዜ፣ በቤልጂየም ብራስልስ ከተማ ህዳር 4 ቀን 2019 ዓ.ም. ሕይወታቸው አልፏል።

የአብሥራ ተፈራ









