ባለፉት በርካታ ዓመታት የአማራ ክልል ልሂቃን ሁለትና ከዛ በላይ በሆነ ጎራ ውስጥ ሆነው ሲተገብሩት የነበረው ፖለቲካዊ አካሄድ ከሕዝብ የደህንነትና የሰላም ጥያቄ ይልቅ እርስ በእርስ ባለመስማማት፣ በተበታተነ አካሄድ እና በውጫዊ ሴራዎች ላይ የተመሰረተ መሆኑ ለከፋ ውድቀት አጋልጧል ተባለ።

ማርእሸት ፀሐዩ እንደገለጸው ምሁራንና ፖለቲከኞች ትኩረታቸው ሕዝቡን የሚጠቅሙ፣ ተቋማዊ የኢኮኖሚ መዋቅሮችን የሚገነቡ እና የሚያገለግሉ ዘላቂ ፕሮጀክቶችን መንደፍ ላይ መሆን ሲገባው፤ በግለሰቦችና በተቋማት መካከል ባሉ አለመግባባቶች ላይ በማተኮር አልፎም የመንግሥት አካላትን በማጠልሸት ማህበረሰቡን ለከፋ ጉዳት ዳርገዋል።
በተለይም ፖለቲካዊ ትግሉና የልሂቃኑ አጀንዳ መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር ሳይጣጣም ሲቀር፥ ዋጋ የሚከፍለው በግንባር የሚገኘውና በባዶ እግሩ በየበረሃው የሚንከራተተው ተራው ወጣት እንጂ ሐሳቡን የሚያመነጨውና የሚያቀናብረው አለመሆኑ ተገልጿል።
እንደ ሀገርና እንደ ክልል እየተሰነዘሩ ያሉ ጥቃቶች በአጋጣሚ የሚከሰቱ ሳይሆኑ በውጭ ኃይሎች ጭምር ስፖንሰር የሚደረጉ እና የተቀናጁ መሆናቸውን በመጠቆም፥ የፖለቲካ አቅጣጫዎች ጤናማ ባልሆኑ መንገዶች ሲመሩ የውስጥ ሰላም ፈርሶ ከውጭ የሚመጡ የጥፋት ሴራዎች በቀላሉ እንዲከናወኑ በር እንደሚከፍትም አመላክቷል።

የክልሉን እና የሀገሪቱን ሰላም በዘላቂነት ለመመለስ፥ የአማራ ልሂቃን ከዚህ ቀደም ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል ሲሰራቸው የነበሩትን ስህተቶች በድጋሚ ገምግሞ፥ በውጤት ላይ የተመሰረተ ተቋማዊ አሰራር መዘርጋት እንዳለበት አቶ ማርሸት ተናግሯል። «ፖለቲካ ማለት ወዳጅን ማብዛትና ጠላትን መቀነስ እንጂ፥ ራስን በራስ ማጥፋትና የገዛ አካል ላይ ተኩሶ ማሳደድ መሆን የለበትም» ሲልም መልእክቱን አስተላልፏል።
በኤንቢሲ ኢትዮጵያ “ጊዜ ግስ” ፕሮግራም ላይ እንግዳ ሆኖ የቀረበው ማርእሸት ፀሐዩ በሀገሪቱ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች፥ በአማራ ክልል የፖለቲካ መዋቅር፣ በልሂቃኑ ስትራቴጂካዊ አካሄዶች እና በሰላም አቅጣጫዎች ዙሪያ ሰፊና ጥልቅ ማብራሪያ ሰጥቷል።
በ – የአብሥራ ተፈራ












