
የቀድሞ የህወሃት አባልና እስከ 2005 ዓ.ም ድረስ የመከላከያ ሰራዊት መኮንን ሆነው ያገለገሉት ኮሎኔል ገብረዋህድ ኃይሉ ( ወዲ ጎአይ) በኤንቢሲ ኢትዮጵያ “ግዜ ግስ” ፕሮግራም ላይ ቆይታ አድርገዋል ።
“መጥፎ ጦርነት እንጂ መጥፎ ሰላም የለም” ያሉት ኮለኔሉ በጠመንጃና በሃይል ስልጣንም ሆነ ሀገራዊ እድገት እንደማይኖር በማስረዳት አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ከእጅ መስጠትና ትግሉን በሰላም ከማጠናቀቅ ውጪ ሌላ አማራጭ የለም ብለዋል ። ለብዙ ዓመታት የተገነባው ነገር በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠፋ ማድረግ እንደማይገባና ተጨማሪ የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ ሰላማዊ መንገድ መከተል እንደሚገባም አሳስበዋልዋል።

ኮሎኔል ገብረዋህድ ኃይሉ! ( ወዲ ጎዐይ)
በቆይታቸውም የትግራይ ሕዝብ ላለፉት ዓመታት ለከፍተኛ መከራና እንግልት የዳረጉትን ዋና ዋና ምክንያቶች እንዲሁም ከጀርባ ያሉ የጥፋት አካላትን ተፅዕኖ በግልጽ አጋልጠዋል ።
ኮሎኔሉ የትግራይ ሕዝብ ተገዶ ወደ ጦርነት የገባው ፣ በሕዝብ ደም ላይ ቆይተው የግል ሀብት ማከማቸት በፈለጉ ራስ ወዳድ የጦር ነጋዴዎች ሴራ እንደሆነም በጥልቀት አስረድቷል።
ከሻዕቢያ ጦርነት በፊት የትግራይ የጦር አበጋዞች ከመደበኛ አበል ውጪ ምንም ዓይነት ካፒታል አልነበራቸውም ሲሉ ነው ኮሎኔል ገብረዋህድ የገለጹት። ይሁን እንጂ ጦርነቱ ለእነዚህ ግለሰቦች ያልተገባ ሀብትን የማከማቸት እድል ፈጥሮላቸዋል ብለዋል ።
ለአብነትም በመከላከያ ሰራዊት ተከቦ እጁን የሰጠው ሜጀር ጀነራል ዮሐንስ ወልደጊዮርጊስን ( ጆን መዲድ) በመጥቀስ፣ ግለሰቡ በአክሱም፣ በመቀሌ እና በሌሎች አካባቢዎች በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ንብረቶችንና ሕንፃዎችን ማካበቱን ገልጸዋል ።
እነዚህ ህገወጥ አካላት የሕዝብ ሀብትና ንብረትን በማውደም ለራሳቸው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሚያካብቱ ስግብግቦች መሆናቸውንም አብራርተዋል።
የጥፋት ሀይሎቹን ድርጊት አሳዛኝ ገጽታ ሲያነሱም፣ የራሳቸውን ልጆች ከአደጋው በማራቅና በተንደላቀቀ ሕይወት ውስጥ እንዲኖሩ በማድረግ ፤በአንጻሩ ግን የትግራይ ወጣቶችን ፣ ሴቶችና አዛውንቶችን ያለ አንዳች ትርጉም ለጦርነት እሣትና ሞት ይዳርጋሉ ብለዋል።
አክለውም የድሃ ወጣቶችን ሕይወት ለግል ጥቅማቸው መስዋዕት ማድረጋቸው ታላቅ የሞራል ውድቀት መሆኑን ኮሎኔሉ በጽኑ ተችተዋል።
በመጨረሻም የትግራይ ሕዝብ ኢትዮጵያዊነቱን ከቶውንም ጥያቄ ውስጥ አስገብቶ እንደማያውቅ እና ኢትዮጵያዊነቱን ሊነጥቁት ሲሉ በጽናት መቃወሙን በማንሳት ፤ ትግራይ ውስጥ አሁን ያለው የፖለቲካና የአስተዳደር ክፍተት ሊቀየር የሚችለው በልማት ብቻ መሆኑን አመላክተዋል ። የህዝቡ ዋና ፍላጎት ልማትና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን መሆኑን ገልፀው፣ መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄዎች በአፋጣኝ በመመለስ የሰላሙን ሁኔታ ማጠናከር እንደሚገባው አሳስበዋል ።
በ ታደለ ገበየሁ












