119ኛው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ቀን “የድል ሰራዊት” በሚል መሪ ቃል በድምቀት ተከብሯል::
ከ2013 ጀምሮ እየተከበረ የሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ቀን፣ ዓላማ ያደረገው አገራቸውን ከጠላት ለመከላከል እና ሰላምን ለማስጠበቅ ሲሉ መስዋእትነት የከፈሉ፣ አካላቸው የጎደለ እና አሁንም በሀገር እና በህዝብ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት የሚመክቱ ጀግኖችን እውቅና ለመስጠት ነው::
ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ባስተላለፉት መልእክት፣ የሃገርን ሉዓላዊነት እና አንድነት መጠበቅ የመከላከያ ሰራዊቱ ባህሪ ሲሆን የአንድን ሃገር መኖር አለመኖር የሚወስነውም ይሄው ሰራዊት ነው ብለዋል፡፡ መስከረም 13 ከግብጽ እስከ ካርቱምና አስመራ የተቀናጀው የሽብር ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ከባድ ሽንፈት ደርሶበት ሸሽቷል ነው ያሉት።
ህዝቡ ህልውናውን ያቆየው፣ ከውስጥም ከውጪም በርካታ ችግሮች ሲፈጠሩ አንድነትን ለመጠበቅ በመታገሉ እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ፣ የጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ወታደራው አማካሪ፣ የተኩስ አመራር ኃላፊ እና ወደር የሌለው ጥቁር አንበሳ የክብር ሜዳይ ተሸላሚ ጀነራል ዓለምሸት ደግፌ ናቸው::
በመረሃ ግብሩ መልእክታቸውን ያስተላለፉት የመከላከያ ሚኒስትሩ መሐመድ እንድሪስ፣ ሰራዊቱ በጦር ግንባር ጠላትን መክቶ ከመመለስ ባሻገር፣ ሀገሩንና ህዝቡን ለሁለንተናዊ ድል፣ ለዘላቂ ሰላምና ለብሩህ እድገት የሚያበቃ ጠንካራ ተቋማዊ አቅም ያለው መሆኑን አመላክተዋል፡፡
አክለውም የመከላከያ ሰራዊት ለሀገር ነጻነት፣ ሉዓላዊነት እና ለህዝብ ሁለንተናዊ ደህንነት ሲል እጅግ ከፍተኛ የሆነ የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ላይ የሚገኝ የሀገር ጋሻና አለኝታ በመሆኑ የዘንድሮው በዓል “የድል ሰራዊት” በሚል መሪ ቃል መከበሩ ሰራዊቱ በርካታ የውስጥና የውጭ ፈተናዎችን በጽናትና በጀግንነት አሸንፎ የወጣ እውነተኛ የድል ባለቤት መሆኑን ያረጋግጣል ብለዋል፡፡
በተካሄደው ጥልቅና አጠቃላይ የሪፎርም ሥራ ተቋሙ በምድር፣ በአየር እና በሳይበር ምህዳር ያለው ሁለንተናዊ የውጊያ እና የደህንነት አቅም በአስተማማኝ ደረጃ ላይ ይገኛል ዛሬ ላይ ሰራዊቱ በዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት እና በቴክኖሎጂ ምጥቀት ራሱን ሙሉ በሙሉ ያደሰ ኃይል መሆኑን አሳውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የራሱን ሉዓላዊነት ከማስከበር ባለፈ፣ የመላው የአፍሪካ ቀንድን እና የቀጠናውን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ማስጠበቅ የሚያስችል ስትራቴጂካዊ ሚና እየተጫወተ እንደሆነ በማስታወስ፣ የእናት ሀገርን ክብርና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ሲሉ ውድ ህይወታቸውን የሰጡ የሰራዊቱ ሰማዕታት በታላቅ አክብሮት ታስበው በመዋል፣ በየበረሃውና በየተራራው በጽናት ለሀገር ዘብ ለቆሙት አባላትም የመከላከያ ሚኒስትሩ ልባዊ ምስጋናቸውን አቀርበዋል።
በመርሃ ግብሩ የመከላከያ ማርች ቡድን ወታደራዊ የሰልፍ ትርኢት ያሳየ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ሙዚቃዊ ድራማ አሳይተዋል፡፡ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሆን በዲጂታል ሚዲያ ለዓመታት በመደገፍ እና ተጽዕኖ በመፍጠር ጉልህ ሚናን ለተጫወቱ አካላትም የክብር አባልነት እውቅና ተሰጥቷቸዋል:: እንዲሁም የመከላከያ ማርች ቡድን፣ የውጪ ሃገራት ወታደራዊ አታሼዎች፣ የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች፣ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ጀግና አርበኞች፣ የሀይማኖት አባቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ባሉበት በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡

















