በ – ሰላም ይልማ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የስራ ዘመኑ መጠናቀቁ አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ባለፉት 4 ዓመታት ከ8 ወራት ያከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራትን አንስቷል። መግለጫውን የሰጡት የሀገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነን ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ የሀገራዊ ምክክር ውጤታማነት የጋራ ትጋት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ የምክክሩን ስነ ዘዴ ማዘጋጀት፣ በሀገሪቱ 1 ሺህ 400 ወረዳዎችን ጋር በመድረስ የምክክር ተሳታፊዎችን ማሳተፉ፣ 4 ሺህ ተመካካሪዎች የተሳተፉበት ሀገራዊ የምክክር ጉባኤውን ማካሄዱ እና ከምክክሩ የተገኙ ምክረሀሳቦችን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማስረከቡ ዋና ዋና ተግባራት መሆናቸው ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የስራ ዘመኑ ጥቅምት 14 2019 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ ለህዝቡ የተሰጡ ምክረሀሳቦች ተፈጻሚነት በ7ኛ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚተገበር መሆኑን አንስተዋል።

ባለፉት ዓመታት በተሰራው የሀገራዊ ምክክር ሂደት በኢትዮጵያ የተፈጠሩ መሰረታዊ የአለመግባባት መንስኤዎችን በውይይት መፍታት እንደሚቻል የታየበት ነው ብለዋል። በሀገራዊ የምክክር ጉባኤው የጸና ሀገረመንግስት ለመገንባት የሚያስችሉ ምክረሀሳቦች የቀረቡበት እና ስኬታማ እንደነበር ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ የተቋቋመለት ዓላማ የተሳካ እንዲሆን በርካታ አካላት ላደረጉት አበርክቶ ምስጋና አቅርበዋል።













