NBC Ethiopia
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰቆጣ ከተማ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፍ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል።
በሰልፉ ላይ የተገኙ ነዋሪዎች መከላከያ ሠራዊት ሕይወቱን ገብሮ ሰላምን የሚያስከብር የሀገር ዋስትና መኾኑን ተናግረዋል።
ከሰልፈኞቹ መካከል የ70 ዓመቷ አዛውንት ወይዘሮ ዋጋየ አድማሴ፣ ወጣቱ ለድጋፍ ሲወጣ እሳቸውም እንደ እናትነታቸው ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን መኾናቸውን ለማሳየት መውጣታቸውን ገልጸዋል።
ወጣት ሃይማኖት አስፋው በበኩሏ መከላከያ ሠራዊቱ ውስጣዊ እና ውጫዊ ጠላቶችን መመከት የሚችል አስተማማኝ የሰላም ዋስትናችን ነው ካለች በኋላ ከሠራዊቱ ጎን በመቆም የባሕር በር ጥያቄያችንን አብረን እናስመልሳለን ብላለች።
የዋግ ኽምራ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዳግም ባይነሣኝ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ተከብራ እንድትቀጥል የሠራዊቱ ሚና ከፍተኛ መኾኑን ጠቅሰዋል።
የዋግ ሕዝብ ሠራዊቱን በነቂስ ወጥቶ በመደገፉ ምሥጋና አቅርበው በቀጣይም ከመንግሥት እና ከሠራዊቱ ጎን በመሰለፍ የባሕር በር ጥያቄያችንን ከዳር ማድረስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።













