NBC Ethiopia
በኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ጂኦፖለቲካዊ ሰማይ ስር ሁልጊዜም አዳዲስ አውሎ ነፋሶች ይነሳሉ። ሀገሪቱ በታሪኳ አያሌ ፈተናዎችንና የውስጥ ግጭቶችን ብታሳልፍም ባለፉት ዓመታት አስተናግዳቸው የማታውቃቸው ውስብስብ ሀገራዊ ውጥረቶች ደግሞ የብዙዎችን ትኩረት ስበዋል።
በኤንቢሲ ኢትዮጵያ «ጊዜ ግስ» ፕሮግራም ላይ እንግዳ ሆነው የቀረቡት ዲፕሎማትና አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ እና የቀጣናውን ስትራቴጂካዊ ውጥረት በጥልቀት አብራርተዋል፡፡
አምባሳደር ሱሌማን እንደገለፁት፣ ህወሓት ከመሰረቱ ጀምሮ ከግጭትና ውጥረት ውጪ በሰላማዊ መንገድ መኖር የማይችል ድርጅ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ በስልጣን በቆየባቸው 27 ዓመታት ብቻ ሳይሆን ከዚያ በፊት በነበሩት የትግል ዓመታትም የተለየ ሀሳብ ያላቸውን አካላት እያገለለና እያጠፋ የመጣ አምባገነን አካሄድ ነበረው ብለዋል።
«ህወሓት ኢትዮጵያን አፍርሶ ትንንሽ ግዛቶችን በመፍጠር እና በትግራይ ሪፐብሊክ ስር የዉሸት መንግስታትን በማቋቋም ሀብታቸውን ለመቆጣጠር እንጂ በእኩልነትና በሰላም በመኖር አያምንም፣» ሲሉ አምባሳደሩ ያብራራሉ።
ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ አምባሳደሩ ሲያብራሩ ዘመቻው የህወሓት የራሱ ዝግጅትና እቅድ ሳይሆን በውጭ ኃይሎች ተገዶና ታዞ የገባበት እንደሆነ ይናገራሉ። የህወሃት ዋንኛው ውድቅት ህዝባዊ ቅቡልነት ማጣቱ ነው ሲሉም ያስረዳሉ፡
ህገወጡ ድርጅት እናቶች እያለቀሱ በግዳጅ ወጣቶችን ስብስቦ በመያዙ በጦርነቱ ላይ ምንም ውጤት አላመጣም፡፡ ወጣቱ እምነትም ሆነ ፍላጐት በማጣቱ የትም ሊደርስ አልቻለም፡፡
ከትግራይም ሆነ ከኢትዮጵያ ህዝብ ልብ ውስጥ ሙሉ በሙሉ በመውጣቱ የቀደመው አይነት ህዝባዊ ድጋፍ አጥቷል፡፡ አሁን ያለው ኃይል የተበታተነ በመሆኑና የአመራር ውድቀት ስለገጠመው የህዝብ ድጋፍ በሌለበት ሁኔታ ወደ ውጊያ መግባት እንደማይችሉ አምባሳደሩ ያብራራሉ።

የህወሓት ትልቁ ሀገራዊ አደጋ በ27 ዓመታት አገዛዙ ወቅት በህዝቦች መካከል የተከለው የጥላቻና የዘረኝነት መርዝ እንደሆነና ድርጅቱ ሀገር ለማፍረስ አስቀድሞ «የሰውን ጭንቅላት መፍታት» እንደሚገባ በማመን በብሔሮች መካከል ጥርጣሬና ጥላቻን በመዝራት ሲሰራ ቆይቷል፡፡
በተጨማሪም የድርጅቱ ታሪካዊ አመጣጥ የትግራይ ህዝብ ትግል የወለደው ሳይሆን የኢትዮጵያን ተፅዕኖ ለማሳነስ ከሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች አጀንዳ ጋር የተሳሰረ ቅጥረኛ አካሄድ እንደነበር ያስረዳሉ። ድርጅቱ ሀገራዊ አላማ ቢኖረው ኖሮ እንደ ባህር በር ያሉ ታሪካዊና ስትራቴጂካዊ ጥቅሞችን አሳልፎ እንደማይሰጥም ይጠቅሳሉ።
ቀጣዩ የመንግስት ስራ አካባቢውን ወደተረጋጋ ሁኔታ ማሸጋገር እና የውጭ ዜግነት ይዞ በሀገር ውስጥ ፖለቲካ ስም መነገድና የጦርነት ልሳን መሆን የክህደት ወንጀል በመሆኑ በህግ መጠየቅ እንዳለባቸው ያነሳሉ፡፡ አያይዘውም በሀገሪቱ ታጣቂና ሰራዊት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በጭራሽ ሊኖሩ አይገባም ሲሉ ምክራቸውን ሰጥተዋል፡፡
በማጠቃለያቸውም ጦርነት በራሱ የመጨረሻ መፍትሔ ሊሆን እንደማይችልና የትኛውም ግጭት በሰላም መጠናቀቅ እንዳለበት ገልጸው በቀጣይ የሚደረጉ ሂደቶች በሙሉ ሌላ ጦርነትን በማይወልድ እና የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም በሚያረጋግጥ መልኩ መጠናቀቅ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በ-የአብስራ ተፈራ












