
ድሬደዋ፣ መስከረም 22/2019(ኢዜአ) :-የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አቶ አብዱላሂ አደንን የአስተዳደሩ ከንቲባ አድርጎ ሾመ፡፡
የድሬደዋ አስተዳደር ምክርቤት 4ኛ የስራ ዘመን 1ኛ ዓመት መስራች ጉባዔ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
ምክርቤቱ አቶ አብዱላሂ አደን ዩሱፍን የአስተዳደሩ ከንቲባ በማድረግ በሙሉ ድምፅ ሹሟል።
አዲሱ ከንቲባም በምክርቤቱ ፊት ህዝብን በታማኝነትና በቅንነትና በፍትሃዊነት ለማገልገል ቃል ገብተዋል።
አዲሱ ከንቲባ አብዱላሂ በወቅቱ፤ በድሬዳዋ በወጣትነት ዘመናቸው ያበረከቱትን አስተዋፅኦ በጉልምስና ዘመናቸው ህዝብን ለማገልገል ኃላፊነት በመውሰዳቸውም ታላቅ ኩራት ይሰማኛል ብለዋል።
ህዝብን መሠረት ያደረጉ እና የዜጎችን መሠረታዊ ጥያቄዎች የሚፈቱ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በላቀ ደረጃ ለመፍታት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በተለይም በአስተዳደሩ ገጠርና ከተማ የተጀመሩ ሁለንተናዊ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን በፍጥነትና በጥራት ማጠናቀቅን ባህል በማድረግ በትኩረት እንደሚሰራም ከንቲባው አረጋግጠዋል።
ከንቲባ አብዱላሂ አደን በቀጣይ የአስተዳደሩን ምክትል ከንቲባ እንዲሁም የካቢኔ አባላት ለምክርቤት ቤቱ ለሹመት እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል።












