
በሳዑዲ ዓረቢያ በከባድ እና አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይገኙ የነበሩ 1 ሺህ 592 ኢትዮጵያውያን ዜጎች ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ተመላሾቹ በሳምንቱ ውስጥ በተካሄደ ዘጠኝ ዙር የአየር በረራ ሀገራቸው የገቡ ሲሆን፣ ሁሉም ወንዶች ናቸው። ከተመላሾቹ መካከል 34 ያህሉ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች እንደሚገኙበትም ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ለተመላሽ ዜጎች በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እና በማቆያ ማዕከላት አስፈላጊው የመጀመሪያ ደረጃ ድጋፍ እና እንክብካቤ እየተደረገላቸው ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪም ተመላሾችን በአስተማማኝ ሁኔታ ከየቤተሰቦቻቸው ጋር የማቀላቀል ስራ እየተከናወነ እንደሆነ ተመልክቷል።
መስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም በተጀመረው በዚህ ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት የማስመለስ ዘመቻ እስካሁን ከ103 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን በሰላም ወደ ሀገራቸው መመለስ መቻሉን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።












