
የ2029 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን የማስተናገድ መብት ለናይሮቢ መሰጠቱ በመላው አፍሪካ ከፍተኛ ደስታን ፈጥሯል።የሁለት ጊዜ የኦሎምፒክ የ10,000 ሜትር ሻምፒዮን የሆነው ታላቁ ኢትዮጵያዊ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ የዓለም አትሌቲክስ ማህበር ማክሰኞ ጠዋት ባወጣው በዚህ “ድንቅ ዜና” መላውን አፍሪካ እንኳን ደስ አለዎት ብሏል።
ይህ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ሊካሄድ መሆኑ ታሪካዊ ክስተት ሲሆን፣ የኬንያ ዋና ከተማ ውድድሩን ለማስተናገድ ከቀድሞ የኦሎምፒክ አስተናጋጅ ከተሞች ከሆኑት ለንደን እና ሮም ጋር ተወዳድራ ማሸነፏን ተከትሎ ነው።
ከሶስት ዓመታት በኋላ የአለማችን ምርጥ አትሌቶች በ48,000 ተመልካች በሚይዘው የካሳራኒ ስታዲየም እንደሚሰባሰቡ ሲሰማ፣ የምስራቅ አፍሪካ ታላላቅ የአትሌቲክስ ኮከቦች በዜናው መደሰታቸው የሚጠበቅ ነበር።
በኬንያ ለዚህ ስፖርት ካለው ከፍተኛ ፍቅር እና ተወዳጅነት አንጻር፣ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች አትሌቲክሱ “ወደ ቤቱ እየተመለሰ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
‘ለአፍሪካ ትልቅ ክስተት’
እ.ኤ.አ. በ2015 የጦር ውርወራ (javelin) የዓለም ሻምፒዮን የነበረው ጁሊየስ የጎ፣ ውድድሩን የማስተናገድ መብት ማግኘቷ “ለአፍሪካ ትልቅ ነገር ነው” ብሏል።
ይህ የ37 ዓመት አትሌት ለቢቢሲ እንደተናገረው፣ “ዓለም ወደ ኬንያ በመምጣቷ በጣም ደስተኛ ነኝ”።
“አፍሪካ ምርጥ አትሌቶችን አፍርታለች፤ ነገር ግን እንደዚህ አይነት ትልቅ ሻምፒዮና በአካል የመመልከት እድል አግኝተን አናውቅም።”
“ይህ ሰዎችን ወደ አፍሪካ የሚያመጣ ክስተት ነው።” “እናም ሰዎች አፍሪካን ያውቋታል።”

ኬንያውያን ለአትሌቲክስ ስፖርት ባላቸው ፍቅር ይታወቃሉ፤ ወርልድ አትሌቲክስ’ ባደረገው ጥናት መሰረት፣ በሀገሪቱ ውስጥ ከተጠየቁት ሰዎች መካከል 68 በመቶ የሚሆኑት ለስፖርቱ ያላቸውን ፍላጎት ‘ከፍተኛ’ እንደሆነ ገልጸዋል።
ኬንያ የ2029ቱን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የማስተናገድ መብት ያገኘችው እንዴት ነው?
ኬንያ በአፍሪካ የመጀመሪያዋ በመሆን የ2029ቱን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታስተናግዳለች
ሁይሌ ገብረሥላሴ፣ ለ2027ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት ሲባል እድሳት እየተደረገለት ባለው የካሳራኒ ስታዲየም ውስጥ የሚኖረው ድባብ “እጅግ የተለየ” እንደሚሆን ይጠብቃሉ።”ይህ በራስህ ህዝብ እና ከተማ ፊት የሚከናወን እጅግ ትልቅ ክስተት ነው” ብለዋል።
“ብዙ ተመልካቾች ወደ ናይሮቢ መብረር ይችላሉ፤ ብዙ ሰዎችም አትሌቶቻቸውን መመልከት ይችላሉ።ነገሩ ድንቅ ይሆናል። እኔ ራሴም ለመመልከት እዚያ እገኛለሁ።
“ልክ እንደ እግር ኳሱ ሁሉ፣ በራስ ሜዳ መጫወት እና ከሜዳ ውጭ መጫወት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። በ2029 ውድድርን ለማሸነፍ ለኬንያውያን እንዲሁም ለኢትዮጵያውያን ይህ ትልቅ ዕድል ነው።”
ኬንያው ሯጭ ፈርዲናንድ ኦማንያላ፣ ሀገሪቱ ትልቅ ሻምፒዮና ስታስተናግድ ማየት “ሁሌም ህልሙ እንደነበር” ተናግሯል።እ.ኤ.አ. በ2007 በኦሳካ በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮና የሴቶች የ800 ሜትር አሸናፊ የነበረችው ጃኔት ጄፕኮስጌይ፣ ይህ “እጅግ አስደሳች” ውሳኔ ቀጣዩን የአትሌቶች ትውልድ እንደሚያነሳሳ ታምናለች።
“ይህ ለወጣቶች እና ለታዳጊዎች ትልቅ ትርጉም አለው፤ ምክንያቱም ህልማቸውን በእጅጉ ከፍ ያደርገዋል” ብላለች።
“ይህ ወጣቶች እና ታዳጊዎች በሜዳቸው ላይ የማሸነፍ ህልም ማለም መጀመር ያለባቸው ወቅት ነው።”
ከውድድር ዓለም ጡረታ ከወጣች በኋላ ወደ አሰልጣኝነት የተሸጋገረችው ጄፕኮስጌይ፣ በሀገራቸው መሬት ላይ ለዓለም ሻምፒዮናነት የመወዳደር ዕድል በማግኘታቸው፣ ለወደፊት ኮከብ አትሌቶች ጠንካራ ግብ እንደተቀመጠላቸው ትናገራለች።
“ከእነዚህ ወጣቶች ጋር ህልም ስንጋራ እና ግቦቻቸውን ስናስቀምጥ ቆይተናል” ብላለች።
“አሁን ያሉት ወጣቶች ችሎታቸውን የሚያሳዩበት መድረክ ይህ ነው።” “እጅግ ተስፋ ሰጪ ለሆኑት አትሌቶቻችን ከፊታችን የሶስት ዓመታት ጊዜ አለን። ይህ ደግሞ ለስፖርቱ ያላቸውን ቁርጠኝነት፣ ትኩረት እና ዲሲፕሊን ጠብቀው እንዲቀጥሉ ለማድረግ ጥሩ መንገድ ነው።
“ከአትሌቶቼ ጋር ስነጋገር ‘ውድድሩ ወደ ቤታችን መጥቷል፤ ስለዚህ እኛም በዚያ የመነሻ መስመር ላይ መገኘት አለብን’ እያሉ ነው።”
“እንደ አፍሪካውያን፣ ትልቅ ነገር ማሰብና አስቀድመን ማቀድ ይኖርብናል። ‘አዎ፣ እንደ ዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ያለ ትልቅ ውድድርን በአፍሪካ ማስተናገድ ይቻላል’ ብለን ማመን አለብን።
“ለኦሎምፒክም እንዲሁ ነው። አፍሪካ በ2010 በደቡብ አፍሪካ የዓለም ዋንጫን አስተናግዳለች፤ ስለዚህ ትላልቅ ውድድሮችን የማስተናገድ አቅም አለን ብዬ አስባለሁ።
“የኦሎምፒክ ውድድርን የማስተናገድ ህልም እናልም፤ እንዲሁም በስፖርት ዘርፍ የዓለም ምርጦችን ወደ አፍሪካ እናምጣ፤ አፍሪካን እንዲሰማትና እንዲደሰቱባት እናድርግ።”
ግብፅ እና ደቡብ አፍሪካ የ2036ቱን ኦሎምፒክ ለማስተናገድ ፍላጎት እንዳላቸው ቀደም ሲል ገልጸዋል።የዬጎን አዎንታዊ አመለካከት ሀይሌ ገብረሥላሴም ይጋራዋል፤ ሌሎች ከተሞች ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማስተናገድ የሚያስችል በራስ መተማመን እንዲያዳብሩ ተስፋ ያደርጋል።
“ይህ በስፖርት ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ እና በፖለቲካም ረገድ ትልቅ ዕድል ነው። አሁን አፍሪካውያን የሚፈልጉትን ማንኛውንም ነገር ማድረግ ይችላሉ” ሲሉ የ53 ዓመቱ አትሌት ተናግረዋል።
“ናይሮቢ ይህንን ሻምፒዮና ማስተናገድ ከቻለች፣ ለምን አዲስ አበባ አትችልም? ለምንስ ላጎስ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኡጋንዳ ወይም ሩዋንዳ አይችሉም?
“በ2029፣ እነሱ (ኬንያ) ውድድሩን በሚያስደንቅ ሁኔታ እንደሚያስተናግዱት መላው ዓለም እንደሚደነቅ አስባለሁ።”
ሳምሶን አበበ












