
በሥነ-ስርዓቱ ላይ የኢ/እ/ፌ ፕሬዝዳንት፣ የካፍ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የፊፋ ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ ኢሳያስ ጅራ፣ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ባሕሩ ጥላሁን፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ የክልል እና ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች፣ የክልል እና ከተማ አስተዳደር ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንቶች እንዲሁም የሚዲያ አባላት በተገኙበት ስትራቴጂው ይፋ ተደርጓል።
በመድረኩን በንግግር የከፈቱት አቶ ኢሳያስ ጅራ ስትራቴጂው ቀጣይነት ላለው የታዳጊዎች ልማት መሠረት እንደሚጥል ጠቁመው ፕሮግራሙ ታዳጊዎችን በውድድር ከማሳተፍም በላይ ትልቅ ሀገራዊ ትርጉም እንዳለው አብራርተዋል። አክለውም የሀገራችንን የወጣቶች እግር ኳስ እድገት በትክክለኛው መንገድ መምራት እንዳለብን በመጠቆም በተለይም በትክክለኛ ዕድሜ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ካልተቻለ የስትራቴጂው ስኬታማነትና ተግባራዊነት አዳጋች እንደሚሆን አጥብቀው አሳስበዋል። ክቡር ፕሬዝዳንቱ አያይዘውም ቀደም ሲል በነበረው አሰራር የነበሩ የዕድሜ ማጭበርበር አሳሳቢ የነበሩ ቢሆንም አሁን ግን በተዘጋጀው አሰራር እና ጥብቅ ቁጥጥር ትክክለኛውን እድሜ መያዝ መቻሉን ገልጸዋል። የስትራቴጂው ትግበራ ስኬታማ እንዲሆን የክልል ቢሮ ኃላፊዎች እና የክልል ፌደሬሽን አመራሮች ሥራውን በባለቤትነት ስሜት ይዘው ወደ ታች ወርደው መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የህክምና ዳይሬክተር እና የስትራቴጂ አማካሪ ዶ/ር ሳሙኤል የሺዋስ በስራቴጂው እና በትግበራው ዙርያ በሰጡት ሰፊ ገለጻ ውድድሩ በ5 ክልሎች ተደራጅቶ በ21 ከተሞች የሚካሄድ መሆኑን አስታውቀዋል። በዕቅዱ መሠረት እያንዳንዱ ከተማ በትንሹ 10 እና ከዚያ በላይ ቡድኖችን የሚያቀፍ ሲሆን በጠቅላላው ከ9,600 እስከ 12,000 የሚደርሱ ታዳጊ ተጫዋቾች ይሳተፉበታል። የከተሞች ውድድር ከተጠናቀቀ በኋላም ሀገር አቀፍ የማጠቃለያ ውድድር የሚካሄድ ይሆናል።
የታዳጊዎችን ብቃት በቅርበት ለመከታተልና ለመመልመል ፌደሬሽኑ በየከተሞቹ ለሚመድባቸው 21 ባለሙያዎች የኮምፒውተር ቁሳቁሶችን በማሟላት እና የስካውቲንግ ስልጠናዎችን በመስጠት ወደ ስራ እንዲገቡ ያደርጋል። ፕሮጀክቱ 105 ሚልየን ብር ዓመታዊ በጀት የሚወስድ ሲሆን የሊጉ ዋና ዓላማ ብቁና ተተኪ ተጫዋቾችን ማፍራት እንዲሁም የተሰጥኦ መሰረቱን ማስፋት እንደሆነ ተገልጿል። ውድድሩንም እስከ ጥቅምት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ለመጀመር አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ዶ/ር ሳሙኤል አብራርተዋል።
ከገለጻው በኋላ ከተሳታፊዎች አስተያየት የተደመጠ ሲሆን በመጨረሻም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከክልል እና ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮዎች እንዲሁም የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ጋር የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል።
ምንጭ የኢ.እ.ፌ












