
7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ምክንያት በማድረግ በዛሬው ዕለት በአማራ ክልል በሁሉም ከተሞች የተካሄደው የብልጽግና ፓርቲ የድጋፍ ሰላማዊ ሰልፍ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ መጠናቀቁ ተገለጸ።
የክልሉ ርዕሰ መዲና ባህር ዳርን ጨምሮ በሁሉም ከተሞች የተካሄደው ታላቅ ህዝባዊ ሰልፍ ያለ ምንም የጸጥታ መደፍረስ በስኬት ተጠናቋል።
ለሰልፉ ስኬታማነትና ፍጹም ሰላማዊ መሆን የጸጥታ ኃይሉ ቀደም ብሎ ያደረገው ከፍተኛ የሰው ኃይል ስምሪትና የሎጀስቲክስ ዝግጅት ቀዳሚውን ሚና ተጫውቷል።
የጸጥታ ሀይሉ አሁን ላይ በክልሉ ከሚስተዋሉ የሰላም ስጋቶች በመነሳትና ተጨባጭ ሁኔታዎችን ባገናዘበ መልኩ አስቀድሞ የሰላም ዕቅዶችን በመቅረጽ፣ ስምሪቱን በከፍተኛ ጥንቃቄና ስልታዊ በሆነ መንገድ ማከናወኑ ተመልክቷል። ይህም በሰልፉ ዕለት የታየውን የጸጥታ መዋቅር የላቀ ጥንካሬና አስተማማኝነት በተግባር ያሳየ ሆኗል።
በሰልፉ ሂደት ላይ በልዩ ሁኔታ የተስተዋለውና ለስኬቱ ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረከተው በጸጥታ ኃይሉና በሰልፈኛው ህዝብ መካከል የነበረው የርስ በርስ ተግባቦትና ቅንጅት መሆኑም ተጠቁሟል።
የጸጥታ ሀይሎች ከህዝብ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ግልጽና ወዳጃዊ በማድረግ፣ ህብረተሰቡ የሰላሙ ቀጥተኛ ባለቤት እንዲሆንና ጥቆማዎችን በፍጥነት በመስጠት የጋራ ጥበቃ እንዲያደርግ አስችለውታል።
ይህ የተቀናጀ ስራ የጸጥታ ኃይሉ ሰላምን ለማስከበር ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነትና የሙያ ብቃት በግልጽ ያሳየበት እንደነበር ተገልጿል።
የጸጥታ ሀይሉ በክልሉ ከተሞች ያሳየው ከፍተኛ የዝግጁነት መንፈስ፣ ቀጣይ ለሚደረገው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫም አስተማማኝ መሰረት የጣለ እንደሆነም ተመላክቷል።
የጸጥታ ኃይሉ ምርጫው ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅና ዜጎች ያለ ምንም ስጋትና መሳቀቅ በነጻነት ወጥተው የሚፈልጉትን አካል መምረጥ እንዲችሉ የሰላም ጥበቃ ስራውን አጠናክሮ ይቀጥላል።
ዜጎች ያለማንም ጣልቃ ገብነት ህገ-መንግስታዊ መብታቸውን ተጠቅመው ድምጻቸውን መስጠት እንዲችሉ ሙሉ የህግ ጥበቃና ከለላ ለመስጠት ተቋማዊ ዝግጅቱ በከፍተኛ ደረጃ መጠናቀቁም ተመልክቷል።
ሰልፉ ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ግንባር ቀደም ሚና ለተጫወቱት ለክልሉ ፖሊስ፣የመከላከያ ሠራዊት፣ ለፌደራል ፖሊስና ለሌሎችም የሰላም አስከባሪ አካላት እንዲሁም የጸጥታ ኃይሉን ስራ በንቃት ለደገፉት ወጣቶችና ለመላው የክልሉ ህዝብ ከፍ ያለ ምስጋና ቀርቧል።












