
ሞጅታባ ኻሚኒ በኢራን ፖለቲካ ውስጥ እጅግ ከፍተኛ ተጽዕኖ ካላቸው ሰዎች አንዱ ቢሆንም፣ በአደባባይ መታየት ግን አይወድም። ንግግር ሲያደርግ ወይም ቃለ መጠይቅ ሲሰጥ አይታይም። አብዛኛውን ስራውን የሚሰራው “ከመጋረጃ ጀርባ” ሆኖ የአባቱን ቢሮ በመቆጣጠር ነው።
ስለ ግል ህይወቱ እና ስለ ሃብቱ የሚወጡ መረጃዎች በጣም ውስን ናቸው። ሆኖም በብሪታንያ ባንኮች ውስጥ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር እንዳለው በምዕራባውያን ሚዲያዎች ይነገራል። በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካ ማዕቀብ ከተጣለባቸው የኢራን ባለስልጣናትም አንዱ ነው።
የፖለቲካ ጉዞው ከልጅነቱ የጀመረው ሞጅታባ፣ በ17 ዓመቱ በኢራን – ኢራቅ ጦርነት ግንባር ድረስ ሄዶ የተዋጋ ሲሆን፣ አሁን ለስልጣን ያበቃውን የደህንነት እና የፖለቲካ መረብ የመፍጠር ጅማሮ ነው ተብሏል፡፡
ሞጅታባ የአባቱ ልጅ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በሃይማኖታዊ እውቀቱም ተቀባይነት ለማግኘት ረጅም እና ስልታዊ ጉዞ አድርጓል። ሞጅታባ ለተከታታይ 15 ዓመታት “ዳርስ-ኢ ካሬጅ” የተሰኘውን ከፍተኛውን የእስልምና የህግ እና የፍልስፍና ትምህርት በማስተማር በኢራን ህግ “ከፍተኛ መሪ” (Supreme Leader) ለመሆን የግድ የሚያስፈልገውን ከፍተኛ የሃይማኖት እውቀት እና ተቀባይነት አግኝቷል።
በኩም (Qom) የሃይማኖት ተማሪዎች መድረክ በኩል በይፋ እንደተነገረው፣ ሞጅታባ በ2022 (እ.አ.አ) የ “አያቶላ” ማዕረግ ላይ ደርሷል። ይህ ማዕረግ ለኢራን መሪነት ዋነኛው ቁልፍ ነው።
ሆኖም ምንም አይነት ይፋዊ የመንግስት ስልጣን ይዞ አለማወቁ፣ ከውጭ ሀገር ባለስልጣናት ጋር ተገናኝቶ አለማወቁ፣ እንዲሁም ስለ ኑክሌር ድርድር ወይም ስለ እስራኤል ያለው አቋም በውል አለመታወቁ የሞጅታባን ሹመት አወዛጋቢ ካደረጉ ነገሮች መሃል ይቆጠራሉ።
ሞጅታባ ኻሚኒ በጦርነት አውድ ውስጥ ስልጣን መያዙ፣ እንደ ብቁ የጦር አዛዥ መሪ ለመሆን እድል እንደሚሰጠው የሚናገሩ ሲኖሩ በሌላ በኩል ደግሞ በኢኮኖሚ ውድቀት ምክንያት “ደካማ መሪ” አድርጎ ታሪኩን ሊያበቃው ይችላል የሚሉም አልጠፉም።
ዘገባው የ-ዩሮ ኒውስ ነው።
በ-ዳንኤል መኮንን












