
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት እና በጣሊያን-አፍሪካ ጉባኤዎች ጥቅሞቿንና ፍላጎቶቿን ያስጠበቁ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ተግባራት ማከናወኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ በሰጡት መግለጫ፥ በአዲስ አበባ የህብረቱ ዋና መሥሪያ ቤት የተካሄደው 48ኛው የአፍሪካ ህብረት ስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ፣ ሁለተኛው የጣሊያን አፍሪካ ጉባኤ እና 39ኛው የህብረቱ መሪዎች ጉባኤ በስኬት ተጠናቋል ብለዋል።
በጉባኤው የተለያዩ ሀገራት መሪዎች፣የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ ቀዳማዊ እመቤቶች፣ የተለያዩ እንግዶችን ጨምሮ ከ20 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች መገኘታቸውን ጠቅሰዋል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከጉባኤው በተጓዳኝ ከተለያዩ ሀገራት መሪዎችና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር ፍሬያማ ውይይቶችን ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጉዳይ የምትጫወተውን ገንቢ ሚና አጠናክራ እንደምትቀጥል ማረጋገጣቸውን አንስተዋል።
በጉባኤው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ከተለያዩ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ውይይት ማድረጋቸውንም ነው አምባሳደር ብርሃኑ ያነሱት።
ኢትዮጵያ በጉባኤው ጥቅሞቿንና ፍላጎቶቻቿን ያስጠበቁ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ተግባራት ማከናወኗን ተናግረዋል።
የጉባኤው ተሳታፊዎች በአቀባበል እና ሽኝት ወቅት መዲናዋን እና የኮሪደር ልማቱን እንዲጎበኙ መደረጉን ጠቁመው፥ ጉባኤው የኢትዮጵያን ገጽታ ይበልጥ የገነባ ነው ብለዋል።
ጉባኤው በስኬት እንዲጠናቀቅ የሀገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙሃን፣ የጸጥታ አካላት፣ የትራፊክ አስተባባሪዎች፣ ሆቴሎችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
የጉባኤው ተሳታፊዎችም በክብር ወደየሀገሮቻቸው ሽኝት እንደተደረገላቸው በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።












