NBC Ethiopia
December 25, 2025
የአማራ ክልል ምክር ቤት ስድስተኛ ዙር፣ አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን እና 11ኛ መደበኛ ጉባዔ በመጀመሪያ ቀን ውሎው የክልሉ ትምህርት ቢሮ የአምስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል ።
በመድረኩ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ተገኝተው በተነሱት የምክር ቤት አባላት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሲሰጡ ትምህርት ከሁሉም የልማት ዘርፎች በተለየ ሰብዓዊ ሀብት ልማት ላይ የሚሰራ በመሆኑ መሪ የልማት ስራ ነው ሲሉ ተደምጠዋል ።

የትምህርት ዘርፉ ከፀጥታ ችግሩ ጀርባ በጥራቱም በሽፋኑም ቀደም ብሎ ችግሮች የነበሩት ዘርፍ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት መሰራት እንዳለበትና አብዛኛውን ጊዜ ትምህርት ሽፋን እንጅ ጥራት ትኩረት መነፈጉን አውስተዋል።

የትምህርት አሰጣጡም ገበያ መር ሆኖ በትኩረት መሰራት አለበት ብለዋል። ለዚህም የት/ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል ልዩ ትኩረት ሰጥተን በተለይ አዳሪ ት/ቤቶች በመገንባት፣ የመፅሐፍ ተማሪ ጥምርታን በማስተካከል፣ እንዲሁም መሰረተ ልማቶችን በማሟላት መስራት ይኖርብናል ሲሉም ተናግረዋል ።

አቶ አረጋ ከበደ በጦርነት የወደሙ ት/ቤቶችን መልሶ በመገንባት ወደ ትምህርት ያልተመለሱ ልጆቻችንን ለመመለስ ሁላችንም ርብርብ ማድረግ አለብን ሲሉም አሳስበዋል።












