December 25, 2025
የሰላም ሚኒስቴር ባዘጋጀው ’’የጋራ ትርክት ለጋራ ሀገር’’ በሚል ርዕስ በቀረበው ሰነድ ላይ የገንዘብ ሚንስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ሠራተኞች ውይይት አካሄደዋል፡፡ በውይይቱ መድረኩ የገንዘብ ሚንስትሩ ክቡር አቶ አህመድ ሺዴ ሀገራችን የረጅም ጊዜ ያልተቋረጠ ታሪክና ስልጣኔ ያላት መሆኑን ገልጸው፣ ሀገራችንን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር መንግሥት በአሁኑ ወቅት ተቀራራቢ የጋራ ትርክት መገንባት አስፈላጊ መሆኑን በማመን ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ጠንካራ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ያለ ጠንካራ ኢኮኖሚ ግንባታ እንደማይሳካ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ ሀገራዊ ምርትን በማሳደግና ድህነትን በመቀነስ ረገድ ትኩረት ሰጥተን በመሥራት ብልፅግናን ዕውን ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡በአንድ ሀገር ጠንካራ ሀገር መንግሥት ተገንብቷል የሚባለው ልዩነቶችን በሰለጠነና ሰላማዊ መንገድ ማስተናገድ ሲቻል፣ መንግሥት የሚያወጣው ሀገራዊ የልማት ፖሊሲዎች በመላ ሀገሪቱ ተፈፃሚነት ሲኖራቸውና ጠንካራ የጸጥታ ተቋማትን በመገንባት ሲቻል መሆኑንም ነው ያነሱት።

በጋራ ትርክት የጋራ ስነ ልቦናን በመያዝ በተሰማራንበት ዘርፍ ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ የበኩላችንን አስተዋጽዖ ማበርክት ይኖርብናል ሲሉ መለክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡












