December 23, 2025
ኢትዮጵያና አሜሪካ በጤናው ዘርፍ የገንዘብ ድጋፍ ሥምምነት ተፈራረሙ፡፡ ኢትዮጵያና አሜሪካ በጤናው ዘርፍ የ 1 ነጥብ 466 ቢሊዮን ዶላር የትብብር የመግባቢያ ሥምምነት ነው በዛሬው እለት የተፈራረሙት፡፡ ሥምምነቱን የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የጤና ሚኒስቴር እና የአሜሪካ ኤምባሲ ተፈራርመዋል፡፡ ይህ ስምምነት ሀገራቱ በጤናው ዘርፍ በጋራ መስራት የሚያስችላቸው ታሪካዊ ስምምነት መሆኑም የተገጸ ሲሆን ለአምስት አመት የሚቆይ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

በዩናይትድ ስቴትስ እና በኢትዮጵያ መካከል የተደረገ ታሪካዊ የጤና ትብብር ስምምነት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የጤና አጋርነት ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ሲሆን ትኩረቱም ዘላቂነት ያለው የጤና ሥርዓት መገንባት መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ስምምነቱ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ራሷን እንድትችል እና የጋራ ኢንቨስትመንት እንዲኖር ያለመ ነው። እንዲሁም በየደረጃው ያሉ የጤና ባለሙያዎችን ማሰልጠን እና መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ማህበረሰብ ተደራሽ ማድረግ ጭምር የሚያስችል ነው ተብሏል።

እንደ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ፣ ወባ እና ሳንባ ነቀርሳ ያሉ በሽታዎችን ከመከላከል ባለፈ ወረርሽኞችን ቀድሞ የመለየት እና የመቆጣጠር አቅምን ለማሳደግ፣ የጤና መረጃ አያያዝን እና የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለትን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መደገፍ ያስችላል። ይህ ስምምነት የኢትዮጵያን የጤና ዘርፍ ይበልጥ ጠንካራ፣ ግልጽነት የተሞላበት እና በራሱ የሚተማመን ለማድረግ ያለመ ሲሆን፤ ለሁለቱ ሀገራት የረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ትልቅ መሠረት ነው።
በ ሰላማዊት ወልደገሪማ












