NBC Ethiopia
December 19, 2025
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልእክታቸው “ዛሬ መካኒሳ አካባቢ የሚገኘውን ቢላሉል ሐበሺ ጎብኝቻለሁ። ተቋሙ የኢትዮጵያ ታሪክ አካል የሆነውን የኢትዮጵያን የእስልምና ጉዞ ከመነሻ እስከ አሁን የሚያሳይ ሙዝየም አደራጅቷል።በሀገራችን የእስልምና ታሪካችንን የሚዘክሩ ሙዝየሞች በጣት የሚቆጠሩ በመሆናቸው፣ ይህ ሙዝየም ታላቅ ዋጋ ያለው ነው። በዚህ ሙዝየም ውስጥ ከመጀመሪያው ሂጅራ አንሥቶ ያለው ታሪካችን ይታያል። ኢትዮጵያ የብዙ ሶሐባዎች ማረፊያ፣ የታላላቅ ዓሊሞች መገኛ፣ የአስደናቂ እስላማዊ ቅርሶች መናኸሪያ ናት።” ብለዋል፡፡

አያይዘውም “ተቋሙ ወጣቶችን በሞያ አሠልጥኖ ለሥራ በማብቃት፣ ችግረኞችን በመርዳት፣ ጥናትና ምርምርን በመደገፍ፣ ለወጣቶች ተስማሚ መዋያ በማዘጋጀት፣ የሚያደርገው አስተዋጽዖ እጅግ ታላቅ ነው። ቢላሉ ሐበሺ ዕድሮች አሁን ከያዙት ዓላማ በላይ በማከናወን የማኅበረሰብን ሕይወት ሊቀይሩ እንደሚችሉ አርአያ ነው። ይሄንን ተቋም በማገዝ ታሪካችንን እንድንጠብቅና ወጣቶቻችንን እንድናበቃ ጥሪ አቀርባለሁ።” ሲሉ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡













