December 9, 2025
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ አገልግሎት ማቀላጠፍ የሚያስችል እና የአሠራር ሒደቶችን በአንድ ስርዓት ያቀናጀ ቴክኖሎጂን ይፋ አድርጓል፡፡

ስርዓቱን ያስጀመሩት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ ባደረጉት ንግገር፤ ቀልጣፋ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በሚሰሩ ስራዎች ዲጂታል አገልግሎትን ማሳደግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ይፋ የተደረገው የተቀናጀ የአምራች ኢንዱስትሪ አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትም በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ብሎም ቀልጣፋና ግልጽ አሰራርን ለመዘርጋት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡ ስርዓቱ የኢንዱስትሪ ምዝገባና አገልግሎት ሂደቶች የሚያካትት፤ የመረጃ ግልጽነትና ትክክለኛነት የሚየረጋግጥ እንዲሁም ኢንዱስትሪዎች ምርታቸውን እንዲያስተዋውቁ እና የግብዓት አቅርቦት ትስስር ለማሳደግ እንደሚያግዝ ነው የተመላከተው፡፡

ቴክኖሎጂው 12 ሞጁሎችን፣ 18 ዋና አገልግሎቶችን እና 40 ንዑስ አገልግሎቶችን ማካተቱ ተገልጿል፡፡ ቴክኖሎጂው በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ልማት ቢሮ አማካኝነት መልማቱ የተጠቆመ ሲሆን ሙከራ ተደርጎ ውጤታማነቱ መረጋገጡ ተነስቷል፡፡

በ – ሰላም ይልማ












