NBC Ethiopia

November 22, 2025
የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የኢንዲስትሪውን ተደራሽነት ለማስፋት፣ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት እና ከምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ለሚመጡ ሰልጣኞችን ተጠቃሚ በማድረግ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ሊገኝበት የሚችል የማሰልጠኛ የልህቀት ማዕከል ሊገነባ መሆኑን አስታውቋል።
ለዚሁ የልህቀት ማዕከል ግንባታ በኪሎሌ ወረዳ በቢሾፍቱ የባቡር ጣቢያ አጠገብ 62 ሄክታር መሬት ተረክቦ በዛሬው ዕለት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት የመሰረት ድንጋይ አኑሯል።

የግንባታ መሰረት ድንጋዩ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ ተቀምጧል።
ኮርፖሬሽኑ አሁን ላይ የአጭር እና የረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ እቅድ በመንደፍ ካለመው ግብ ለመድረስ የባቡር የመሠረተ – ልማት ግንባታ እና የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠትን ጨምሮ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል።
ኮርፖሬሽኑ በኢትዮጵያ ዋና ዋና የተባሉ የልማት ቀጠናዎችን ከሁሉም አጎራባች ሀገሮች ጋር የሚያስተሳስር ዘመናዊ የባቡር መሰረተ ልማት እያከናወነ እንደሚገኝ ነው የጠቆመው።

ከዚህም ባሻገር የምድር ባቡር ኢንዲስትሪውን ከውጭ ጥገኝነት ለማላቀቅ የሚያግዝ የቴክኖሎጂ ሽግግር ስትራቴጂ መንደፉንም አመልክቷል።
በዚሁ ሂደት በባቡር ዘርፉ በራስ አቅም የሰለጠኑ ብቁ የሰው ኃይል በሀገር ውስጥ እያሰለጠነ ተተኪ ባለሞያዎችን በማፍራት ላይ እንደሚገኝም ገልጿል።

በ እየሩሳሌም ዓለሙ
ከቢሾፍቱ ከተማ












