የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) በክልሉ የሚከበረው 20ኛው የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓል ህብረብሄራዊነትን እንደሚያጠናክር ተናግረዋል።
ርዕሰ መተዳድሩ ለበዓሉ እየተደረገ የሚገኘው የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ብሎም የክልሉን አጠቃላይ ሁኔታ አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ምስረታውን ሁለት ዓመታት ያደረገው ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በዓሉ እንዲያዘጋጅ በፌዴሬሽን ምክር ቤት መመርጡ በክልሉ በርካታ የልማት ስራዎችን ለማጠናከር እንደሚያግዝ ተነስቷል።
የህዝቡን አንድነት ለማረጋገጥ እንዲሁም ህዝብ ለህዝብ የሚያስተሳስሩ የጋራ ትርክትን በማስረጽ ህዝብ ለህዝብ ለማስተሳሰር ፋይዳ የጎላ ስለመሆኑ ነው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድ እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) የተናገሩት።
እንዲሁም በክልሉ የልማት ኢንሼቲቮችን ለማጠናከር እንደሚያግዝ የተገለጸ ሲሆን ክልሉ ያለውን ጸጋ በመለየት በግብርና፣ኢንዱስትሪ ፣ ቱሪዝም፣ በማዕድን እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይ ፕሮጀክትን በፍጥነትና በቅልጥፍና የማጠናቀቅ ሂደት ተግባራዊ መደረጉን የጠቆሙት የክልሉ ፕሬዝዳንት በሁለት ዓመት ለማጠናቀቅ የታቀደባቸውን ፕሮጀክትን በ6 ወር ለመጨረስ እየተሰራ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።
ህብረተሰቡ ካለው ፍላጎት አንጻር መፍጠንና መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል። ኢትዮጵያ በርካታ ፕሮጀክቶች እውን ባደረገችበት ወቅት የሚከበረው 20ኛው የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓል ለየት ያለ ቦታ የሚሰጠው ስለመሆኑ ተንጸባርቋል።
ከሆቴል እስከ መንገዶች የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸው የተነሳ ሲሆን ከ4500 በላይ እንግዶችን ማስተናገድ የሚችሉ ሆቴሎች እንዲሁም በዓሉ የሚስተናገድበት ስቴዲየም እስከ 35 ሺህ ሰዎችን የማስተናገድ አቅም እንዳለው ተገልጿል።
በ – ሰላም ይልማ












