ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና ቭላድሚር ፑቲን በሃንጋሪ የሚገናኙበት ጊዜ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል ተባለ።
ሮይተርስ ከዋይት ሀውስ ምንጮች አገኘሁት ያለው መረጃ መሪዎቹ በቅርቡ በቡዳፔስት መገናኘት እንደማይችሉ ያመላክታል። የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ እና የአሜሪካው አቻቸው ማርኮ ሩቢዮ በስልክ መወያየታቸውም ይታወሳል።
ሚኒስትሮቹ ጥሩ ውይይት ማድረጋቸውንም የሲ ኤን ኤን ዘገባ ይጠቁማል። በሌላ በኩል የሩሲያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ሪያብኮቭ አሁንም መሪዎቹ እንዲገናኙ አስፈላጊ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው የሚል ሀሳብ ሰጥተዋል።
ጉዳዩን ለመበጥበጥ የምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎች የጀመሩት አሳሳች መረጃ ነውም ሲሉ አሳስበዋል ሪያብኮቭ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ማሪያ ዛኻሮቫ ስሜ አይጠቀስ ያለውን ”መረጃ አቀባይም” አጣጥለዋል።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና ቭላድሚር ፑቲን ከቀናት በፊት በስልክ ሁለት ሰዓት ተኩል ገደማ ማውራታቸውም ይታወሳል። ፕሬዚዳንቶቹ በቡዳፔስት ሀንጋሪ ተገናኝተው ካልመከሩ የዩክሬኑ ጦርነት አሁን ካለው ተወሳስቦ ሊቀጥል እንደሚችልም እየተነገረ ነው።
ዘገባው የኤን ቢ ሲ ኒውስ ነው
በ-ቢኒያም ካሴ












