የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የሆኑት ሲቲ እና ጄፒ ሞርጋን የኢትዮጵያን የካፒታል ገበያ ልማት ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን አስታወቁ።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብስባ በዋሺንግተን ዲሲ ተካሄዷል። የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ ከስብሰባው ጎን ለጎን የአሜሪካ ግዙፍ የፋይናንስ ተቋማት ከሆኑት ጄፒ ሞርጋን እና ሲቲ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።
የሲቲ የመንግስት የባንክ አገልግሎት ዘርፍ ከፍተኛ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄይ ቫርኪይ እና የጄፒ ሞርጋን ማኔጂንግ ዳይሬክተር ኦሊቨር ኢዌክ በውይይቱ ላይ ተገኝተዋል። ውይይቱ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳ፣ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እና ዘላቂ የኢንቨስትመንት ኢኒሼቲቮች መደገፍ የሚቻልባቸው የፋይናንስ አማራጮች ላይ ያተኮረ ነው።
የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት ለመፍጠር ያላትን ቁርጠኝነት ገልጸው፤ እየተደረጉ ስላሉ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሞች ገለጻ አድርገዋል።
አቶ አሕመድ ለሁለቱ ተቋማት አመራሮች የኢትዮጵያን ዘላቂ እዳ አስተዳደር የመፍጠር ጥረቶች፣ የውጭ ምንዛሬ ገበያ ሪፎርሞች እና የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድ ትግበራ አስመልክቶም ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ሚኒስትሩ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና የግሉ ዘርፍ አጋሮች የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን እና የማይበገር አቅም የመገንባት ስራ በመደገፍ ረገድ ያላቸውን ቁልፍ ሚና አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
የሲቲ እና የጄፒ ሞርጋን ከፍተኛ አመራሮች የፋይናንስ ተቋማቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ሁለቱ የፋይናንስ ተቋማት ለኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ልማት እና የፋይናንስ መዋቅሮች ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። ሁለቱ ወገኖች ከፍተኛ ደረጃና የቴክኒክ ውይይቶችን ለማድረግና ትብብራቸውን ለማጠናከር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።












