የአውሮፓ ታላላቅ ቡድኖች በጨዋታ 6 ተጫዋቾችን ቀይሮ ለማስገባት በሚያስችል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተወያዩ።
የአውሮፓ እግር ኳስ ክለቦች ማህበር ባሳለፍነው ሳምንት በጣሊያን ሮም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጓል። በውይይቱ በአጀንዳነት ባይያዝም በአውሮፓ ታላላቅ ቡድኖች በተለይም በእንግሊዝ ክለቦች በጨዋታ 6 ተጫዋቾችን ቀይሮ ማስገባትን የተመለከተ ውይይት መደረጉን ቢቢሲ ዘግቧል።
በጨዋታዎች መደራረብ ሳቢያ በተጫዋቾች ላይ የሚፈጠርን ጫና ያቃልላል በሚል ሃሳቡን ካነሱ ቡድኖች መካከል ማንችስተር ሲቲ፣ ማንችስተር ዩናይትድ፣ ሊቨርፑል እና አርሰናል እንደሚገኙበት ተጠቁሟል።
ክለቦቹ ከ6 ተጫዋቾች ቅያሪ በተጨማሪም በጨዋታ ቀን የሚያስመዘግቡት የቡድን ስብስብ ቁጥራቸው ከ25 ወደ 28 ከፍ ሊል ይገባልም ብለዋል። በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ አሁን ላይ የሚታየው የ5 ተጫዋቾች ቅያሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ የተደረገው የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ እንደነበር አይዘነጋም።
በ2021-22 የውድድር አመት ወደ ነበረበት የ3 ተጭዋቾች ቅያሪ ቢመለስም ክለቦች በሰጡት ድምጽ መነሻነት ከ2022-23 ጀምሮ የ5 ተጫዋቾች ቅያሪ በቋሚነት ተግባራዊ ተደርጓል።
በ-አልፈሪድ ነስሮ












