October 5, 2025
የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የጀመረውን የሪፎርም ሥራ ዲጂታላይዜሽን ማብሰሪያ እና የአዲስ ሕንጻ ምረቃ መርሐ ግብር የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፣ ፖሊሰ በትንሽ በትልቁ እጅ መንሻ ከፈለገ መለዮውን ረስቶታል ማለት ነው፡፡ “ፖሊስ ልቡ፣ አስተሳሰቡ እና እጁ ከጽንፈኝነት፣ ጎጠኝነት እና ሌብነት የፀዳ መኾን ይኖርበታል” ነው ያሉት።

ትናንት “ኢትዮጵያ ትቀጥላለች አትቀጥልም” ትንቅንቅ ውስጥ በነበርንበት ወቅት ሁሉ የፀጥታ ኀይሉ ውድ ዋጋ ከፍሏል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የዛሬው ሪፎርም የትናንቱ ብርቱ ተጋድሎ ውጤት እንደኾነም ጠቁመዋል።
ኤርጎኖሚክስ የለውጡ መንግሥት አንዱ የትኩረት መስክ ነበር ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ምቹ የሥራ አካባቢ የመፍጠር ለውጥ ከራስ ጽዳት ይጀምራል ከሚል እሳቤ የመነጨ እንደኾነም አንስተዋል። በክልሉ በርካታ ተቋማት ላይ የሚታየው የለውጥ ጅምርም አበረታች ነው ብለውታል።

የክልሉ ሕዝብ በሁለት የትውልድ መንታ ተጋድሎ ላይ የሚገኝ ነው፤ ባዕዳ እና ባንዳን የማጽዳት እንዲሁም ድህነት እና ኋላቀርነትን ታሪክ የማድረግ ትግል እንደኾነም አንስተዋል።
የአማራን ሕዝብ ከኢትዮጵያዊነት ማማ እና ካስማ ለማውረድ የሚደረገው ሙከራ ትናንት እንዳልተሳካ ታይቷል፡፡ ዛሬም አልተሳካም፤ ነገም አይሳካም ያሉት አቶ ተመስገን፣ በእያንዳንዷ እኩይ ተግባራቸው የክልሉን ሕዝብ ዋጋ ማስከፈላቸው ግን አልቀረም፡፡ ስለዚህ የለውጥ ሥራዎቹ አስፈላጊነትም የክልሉን ዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላም ባጠረ ጊዜ ለማምጣት ያለመ ነው ብለዋል።

መለዮለባሽ ተጠሪነቱ ሕዝብ ለመረጠው አካል ነው፡፡ ከዚያ ሲያፈነግጥ ግን ምን ዓይነት ዋጋ እንደሚያስከፍል ብዙም ሳንርቅ ትናንት ከራሳችን ዛሬ ደግሞ ከጎረቤቶቻችን አይተናል ነው ያሉት አቶ ተመስገን፣ አያይዘውም ተቋሙ ከለውጥ ሥራዎቹ ጎን ለጎን ክልሉን ከቀሪ ባዕዳ እና ባንዳዎች ማጽዳት ይኖርበታል ብለዋል። ዛሬ የፀዳ እና ምቹ የሥራ አካባቢ ያሳየን የክልሉ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ በቀጣይም ላመነበት ቃል እና ተልዕኮ መስዋዕትነት መክፈልን የሚደፍር፤ ለሕዝብ ክብር ሲባል ራሱን ቅድሚያ የሚያሳልፍ ሠራዊት መገንባት ግድ ይለዋልሲሉ መልእክታቸውን አስተላለፈዋል፡፡
ክልሉን የሚመጥን ፖሊስ መገንባት የቀጣይ ጊዜ ተልዕኮ ነው፤ ጠላት የሚፈራው እና ሕዝብ የሚመካበት የፖሊስ ሠራዊት መገንባት አለበትም ብለዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል ሲል የአማራ ኮሚዩኒኬሽን ያደረሰን መረጃ ያመለክታክል፡፡












