በአፍሪካ ዘላቂና በራስ አቅም የተመሰረተ የማህበራዊ ጥበቃ ሥርዓትን ለማረጋገጥ የላቀ አህጉራዊ ትብብርና ትጋት ወሳኝ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጌጎ ተስፋዬ(ዶ/ር) ገለጹ።
ለተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የማህበራዊ ጥበቃ ዘርፍ ተወካዮች ማህበራዊ ጥበቃ ለዘላቂ ልማትና ደህንነት የተሰኘው ዓለም አቀፍ ስልጠና በኢትዮጵያ መስጠት ተጀምሯል።

ዓለም አቀፍ የስልጠና መርሃ ግብሩ በስዊድን የልማት ኤጀንሲ የሚደገፍ ሲሆን ሀገራት በማህበራዊ ጥበቃ ዙሪያ የተሻለ አቅም ገንብተው ውጤታማ እንዲሆኑ ለማገዝ እ.ኤ.አ ከ2019 ጀምሮ ወደ ሥራ ገብቷል።
በአዲስ አበባ የተጀመረው የሥልጠና መርሃ ግብር ላይ ከኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ሞዛምቢክና ዚምባብዌ የተውጣጡ ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በገጠርና በከተማ በተዘረጋው የልማታዊ ሴፍቲኔት መርሃ ግብር ስምንት ሚሊዮን ዜጎች እየተጠቀሙ መሆኑን ገልጸው በዚህም ከተረጂነት ለመላቀቅ የተቀመጠው ሀገራዊ ግብ እንዲሳካ ርብርቡ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብርም ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ ደረጃ ሞዴል እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ የማህበራዊ ጥበቃ ውጤታማ እንዲሆን ሚኒስቴሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በተናበበ መልኩ መሥራቱ ውጤታማ እንዲሆን ማስቻሉንም አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር ማግነስ ሊናርሰን በበኩላቸው፤ የማህበራዊ ጥበቃ ሥራዎችን ማጠናከር አካታች ሥርዓትን እውን ለማድረግ አወንታዊ ሚና እንዳለው ተናግረዋል። መሰል የስልጠና መርሃ ግብሩም በሀገራት መካከል የልምድ ልውውጥ እንዲጠናከር የተሻለ አውድ እንደሚፈጥር ያላቸውንም እምነት ገልጸዋል።

ስዊድን በማህበራዊ ጥበቃ ዙሪያ በርካታ ልምዶች እንዳሏት ገልጸው፥ ይሄንን ልምዷን ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።












