የመስቀል ደመራ በዓል በመስቀል አደባባይ በተለያዩ ሀይማኖታዊ ክዋኔዎች እየተከበረ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያሪክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ መስቀል ለሰው ልጆች ሰላምና ደህንነት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል። የመስቀል በዓል ስናከብር ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች የከፈለውን ዋጋ የምናስበት እና ለሰላማችንና ለደህንነታችን ዋስትና ከመስቀሉ ሌላ አለመኖሩን የምንረዳበት ነው ብለዋል።
ፍጹምና ዘላቂ ሰላምን የምንሻ ከሆነ በመስቀሉ ቃል እንመራ፤ መስቀል ይቅርታን፣ እርቅን፣ እኩልነትና ፍትህን የምናረጋግጥበት መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል ነው ያሉት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ። የመስቀሉ ትርጉም አንድነትና ፍቅር የሚሰብክ በመሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ እርስ በእርስ ከመጠፋፋት ይልቅ በአብሮነትና በጋራ ተቻችለን መኖር ይገባል ብለዋል።
እንዲሁም የሚታዩ አለመግባባቶችን በይቅርታና በመወያየት መቅረፍ አለብን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
Source:
@NBCEthiopia
Via:
NBCEthiopia












