የመስቀል ደመራ በዓል በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ኃይማኖታዊ ትውፊትና ሥርዓቱን ጠብቆ በድምቀት በመከበር ላይ ይገኛል።
በዘንድሮው ክብረ በዓል ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ብጹዓን አባቶች እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ታድመዋል።
የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ አበባ እምቢአለ፣ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ የልዩ ልዩ አገሮች አምባሳደሮች፣ ጎብኝዎች ተገኝተዋል።
በሥነ-ስርዓቱም በአዲስ አበባ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያንና አድባራት የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራንና ሊቃውንት ኃይማኖታዊ ኅብረ ዝማሬን በማቅረብ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
የመስቀል ደመራ በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ ኃይማኖታዊ እሴትና ሥርዓታቸውን ጠብቀው በአደባባይ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ ነው።
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) የሰው ልጅ ወካይ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን ማስመዝገቧ ይታወቃል፤ የመስቀል ደመራ በዓል አከባበርንም የማይዳሰስ የዓለም ቅርስ አድርጎ መመዝገቡ ይታወሳል።












