የኢትዮጵያ መድሀኒትና የህክምና መገልገያዎች አምራቾች ዘርፍ ማህበር ከአንድ ቢሊየን ብር በታች ዋጋ ያላቸው ህክምና ግብአቶችን ከዚህ ቀደም ለገበያ እያቀረበ የነበረ ሲሆን ባለፉት ሦስት አመታት በተከናወኑ ተግባራት ወደ 15 ሚሊየን ማሳደግ መቻሉን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መድሀኒትና የህክምና መገልገያዎች አምራቾች ዘርፍ ማህበር 22ኛ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ፣የጤና ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት አመራሮች፣ የግል የመድሀኒት አምራችዎች ፣ የአጋር ድርጅቶችና አጋር አካላት በተገኙበት እያካሄደ ይገኛል።
የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዳንኤል ዋቅቶሌ በጉባኤው እንደገለፁት ሀገሪቷ ከዚህ ቀደም ለመድሀኒቶችና ለህክምና መገልገያዎች ግዢ ስታወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪን በመቀነስ ምርቾቹን ሀገር ውስጥ በማምረት ስለመቻሉ አንስተዋል።
በተለይ የኮቪድ ወረርሽን መከሰትን ተከትሎ ለመድሀኒቶችና ለህክምና መገልገያዎችን በሀገር ውስጥ አንዲመረቱ መነሻ መሆኑን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ በዚህም በዘርፉ የተደረገው የፖሊሲ ማሻሻያ በሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ሊያሳድግ ችሏል ብለዋል።
የ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ላለፋት ሦስት ተከታታይ አመታት መዘጋጀት ደግሞ ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆን በማድረግ የራሱን አስተዋጽኦን ማበርከቱን ፕሬዚዳንቱ አንስተዋል።
የጤና ሚኒስቴር የሀገር ውስጥ የመድሀኒት አምራችዎችን በማበረታታት በሀገር ውስጥ የሚመረቱ መድሀኒቶችን በተሻለ ደረጃ ተመርተው እንዲቀርቡ ለማድረግ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ ገልጸዋል።
ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ መድሀኒቶችንና ህክምና መገልገያዎችን በሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ማሳደግ ከህልውና ጋር የተቆራኘ እንዲሁም የሉአላዊነት መገለጫ ነው ብለዋል። የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በበኩላቸው በኢንዱስትሪ ዘርፉ የሀገር ውስጥ ምርቶችን ለማሳደግ የተወሰዱ እርምጃዎች አመርቂ ውጤቶችን እያስገኙ መሆኑን ገልፀዋል።
ባለፈው በጀት አመት 4 ነጥብ 53 ቢሊየን ገንዘብን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉን ያነሱት ሚኒስትሩ በውጭ ምንዛሬ የሚገቡ መድሃኒቶችንና የሕክምና መገልገያዎችን በሀገር ውስጥ ለሚያመርቱ ድርጅቶች አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ በአመታት ውስጥ የተሰተዋሉትን ለውጦችን ለማሳደግ መንግስት የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በማረጋገጥ የግል አምራቾች የሀገርን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ አበክረው ሊሰሩ አንደሚገባ አሳስበዋል።
በሀሴት ኃይሉ












