የየካ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የመስቀል ደመራና ኢሬቻ በዓላት ባህላዊና ሀይማኖታዊ እሴቶችን በጠበቀ መልኩ እንዲከበሩ ውይይት አደረገ፡፡
በዓላቱን የገቢ ምንጭ በማድረግ በሰላም እንዲከበሩ ሀይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ ሀዳ ስንቄዎችና ፎሌዎች በተገኙበት ከአጎራባች ሸገር ሲቲ ነዋሪዎች ጋር ውይይት ተካሂዷል። የዘንድሮው መስቀልና ኢሬቻ በዓላት ሲከበሩ ሀገራዊ አንድነትን ባጠናከረ መልኩ እንዲሆንም በመድረኩ ተነስቷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመስርያ ቦታዎች ኤጀንሲ ምክትል ኃላፊ ሰብለ ታደሰ መስቀልና ኢሬቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ በዓል በመሆኑ ኃይማኖታዊ እና ባሕሉን በጠበቀ መልኩ ማክበር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የየካ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍጹም ኃይሌ በበኩላቸው በዓላቱ በሰላም ተከብረው እንዲያልፉ ከክፍለ ከተማው ነዋሪዎችና ከሀይማኖት አባቶች ጋራ መወያየት አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው መስቀልና ኢሬቻ አንድነትን ሰላምን የሚሰብኩ የአደባባይ በዓላት ናቸው በማለት በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን እንግዶችን በሚገባ ለማስተናገድ መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በ-አማኑኤል ምትኩ












