የ2018 የደመራና የመስቀል በአል በሰላም እንዲከበር የሀይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና የጸጥታ አካላት በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለፀ።
በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በየአመቱ በድምቀት የሚከበረው የደመራና የመስቀል በዓል በሰላም ተከብሮ እንዲያልፍ በቂ ዝግጅት መደረጉ የተገለፀ ሲሆን ምእመኑ በአሉ በሰላም እንዲከበር በጋራ መስራት እንደሚገባቸው ነው የተገለፀ።
የመስቀል በአል በርካታ ምእመናን በአደባባይ ወጥቶ የሚያከብሩ እንደመሆኑ መጠን በዓሉ ሀይማኖታዊ እሴቶችን እና ትውፊቶች በጠበቀ መልኩ ለማክበር ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ሀገረስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ህርያቆስ ገልጸዋል።
መሰቀል የሰላም በአል ነው ያሉት ሊቀ ጳጳሱ በዓሉ በሰላም፣ በፍቅርና በአንድነት ተከብሮ ያልፍ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል።
የመስቀል በአል ከሀይማኖታዊ ትውፊት ባሻገር በሀገር ግንባታ፣ በቱሪዝምና በኢኮኖሚ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው ያሉት የአዲስ አበባ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸኃፊ መጋቤ ታምራት አበጋዝ በዓሉ ያለ አንዳች የጸጥታ ችግር ለማክበር በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
የዘንድሮው የመስቀል በዓል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተመረቀበት ማግስት የሚከበር በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ሲሉ የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሀላፊ ሊድያ ግርማ ገልጸዋል።
በአለም የማይዳሰሱ ቅርስ የተመዘገበውን የመስቀል በአል ሀይማኖታዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ ለማክበር በጋራ እየተሰራ ነው ያሉ ሲሆን በአሉን ተገን አድርገው ሁከት ለመፍጠር የሚሞክሩ አካላትን በጋራ በመተባበር ማጋለጥ ይገባል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ እና ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጋር በመተባበር የ2018 የደመራና የመስቀል በዓል አስመልክቶ ውይይት ተካሂዷል።
በ-ሰላማዊት ወልደገሪማ












