በቻምፒዮንስ ሊግ ፒኤስጂ አታላንታን ካሸነፈበት ጨዋታ አስቀድሞ በተነሳ ሁከት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ጉዳት አጋጠመ።
ፓሪስ ላይ ከተደረገው ጨዋታ አስቀድሞ በስታዲየሙ አቅራቢያ በፒኤስጂና አታላንታ ደጋፊዎች መካከል በተነሳ ነውጥ የአካል ጉዳት ያጋጠማቸው ደጋፊዎች መኖራቸው እና በግለሰብ እና መንግስት ንብረት ላይ ውድመት መድረሱን ዘ ሰን ዘግቧል።
የከተማው ፖሊስ ብጥብጡን አስነስተዋል ያላቸውን 19 ደጋፊዎች በቁጥጥር ስር አውያለሁ ያለ ሲሆን፤ አሁንም በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት ያደረሱትን በማደን ላይ እንደሚገኝ ገልጿል። ጸብ በማስነሳት የጣሊያኑ ክለብ አታላንታ ደጋፊዎች ቢወነጀሉም፤ የፒኤስጂ ጽንፈኛ ደጋፊዎች እንዳባባሱት ተገልጿል።
በስታዲየሙ አካባቢ የሚገኙ የመንግስት ህንጻዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው፤ የግለሰብ ተሽከርካሪዎችም በእሳት እንደተቃጠሉ የፖሊስ መግለጫ አመላክቷል። ፒኤስጂ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ባወጣው መግለጫ በሁከት የተሳተፉ ደጋፊዎቹን በመለየት ላይ እንደሚገኝ በመግለጽ፤ እድሜ ልክ ወደ ሜዳ እንዳይገቡ እግድ እንደሚያስተላልፍ ገልጿል።
አታላንታም በተመሳሳይ በአመጹ የተሳተፉ ደጋፊዎቹን በመለየት ላይ መሆኑን አስታውቋል።
በ-አልፈሪድ ነስሮ












