መንግሥት በሞተር የሚሰሩ ጀልባዎች ከቀረጥና ታክስ ነጻ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ መፍቀዱ የውሃ ቱሪዝምን ለማሳደግ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ ገለጹ።
ኢትዮጵያ በርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም መስህብ አማራጮች ቢኖሯትም በውስን ዘርፎች ላይ ብቻ በማተኮር ስትሰራ መቆየቷ ይታወቃል፡፡ ለዘርፉ ዕድገት እምቅ አቅም ያለውን የውሃ ቱሪዝምን በአግባቡ ለመጠቀም የገንዘብ ሚኒስቴር በሞተር የሚንቀሳቀሱ ጀልባዎች ከቀረጥና ታክስ ነጻ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ፈቅዷል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ እንደተናገሩት፤ ከለውጡ ወዲህ የቱሪዝም ዘርፍ ለሀገር ኢኮኖሚ ያለውን አስተዋፅኦ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶቷል። ይህም መንግሥት የቱሪዝም ዘርፉን ከዕድገት ምሰሶዎች አንዱ በማድረግ የፖሊሲ እና የተለያዩ ድጋፎችን እንዲያገኝ ማድረጉን ገልጸዋል።
የሞተር ጀልባዎች ከቀረጥና ታክስ ነጻ እንዲገቡ መፈቀዱ መንግሥት ለዘርፉ እድገት ቀጣይነት የሰጠውን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
ለቱሪዝም መዳረሻ ልማት መስፋፋት ከሰጠው ትኩረት ባሻገር ለውሃ ቱሪዝም መስፋፋት እና የውሃ ላይ ስፖርቶችን ለማልማት ትልቅ ትኩረት መስጠቱን እንደሚያሳይ ገልጸዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡












