ኢትዮ ቴሌኮም አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በመላው ሀገሪቱ የበጎ አድራጎት ስራዎችን አከናውኗል። ተቋሙ “ለነገ ተስፋዎች” በሚል መርሃ ግብር ከ98.8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ 960ሺህ የመማሪያ ደብተሮችን ለ80ሺህ ተማሪዎች ድጋፍ አድርጓል።

ኩባንያው የዘንድሮን ጨምሮ ባለፉት ስድስት ተከታታይ ዓመታት “ለነገ ተስፋዎች” በሚል መርሃ ግብር በመላው የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚገኙ እና አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ ታሳቢ ያደረገ የመማሪያ ደብተር ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገልጸዋል።
በአጠቃላይ እስከ አሁን በአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች ውስጥ ለሚማሩ 373 ሺህ ተማሪዎች ከ320.8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ድጋፍ መደረጉ ተመላክቷል።
በተጨማሪም “በጎነት” የሚል መርሃ ግብር የዘንድሮውን ጨምሮ ባለፉት አራት ተከታታይ ዓመታት በመላው የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚገኙ 117 የበጎ አድራጎት ተቋማት ከ78.8 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አማድረጉን አስታውቋል፡፡












