ተቋማት ጥራት ያለውና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የህዝቡን እርካታ ለመጨመር ሊተጉ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ ገለጹ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ISO 9001-2015 የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት የምስክር ወረቀት አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት በአዲስ አበባ ተካሂዷል። ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ በዚሁ ወቅት፤ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በዓለምአቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለውን ዕውቅና ማግኘቱ የትጋቱ ውጤት ነው ብለዋል።

የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርሙ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ተቋማት በጥራት ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ማሟላት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከተቋቋመ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሥራ ጥራትና ቅልጥፍና ትኩረት ሰጥቶ መሥራቱን አድንቀዋል። ተቋሙ በቀጣይም ለተገልጋዮች ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት በመስጠት ዓለም-አቀፋዊ ተወዳዳሪነቱን አስጠብቆ እንዲቀጥል አጽንኦት ሰጥተዋል።
የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት (ISO 9001-2015) ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው መለኪያ መስፈርት ሲሆን ምርቶች ወይም አገልግሎቶች የጥራት ደረጃቸው ዓለም-አቀፍ ተቀባይነት እንዲያገኝ ያደርጋል።
በመድረኩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል፣ የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡












