ዓለም አቀፍ በረራዎች ከአዲስ አበባ በተጨማሪ የክልል ኤርፖርቶች ማስተናገድ ሊጀመሩ መሆኑን የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን አስታወቀ።
በባለስልጣኑ የአየር ትራንስፖርትና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች አማካሪ አቶ እንደሻው ይገዙ ባቀረቡት ሪፖርት፣ በ2018 ዓ.ም በረራዎችን ከአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በተጨማሪ በሌሎች የሃገሪቱ ክልል ኤርፖርቶች ማስተናገድ እንደሚጀመር ተናግረዋል።
ከሀገር ውጭ የሚደረጉ በረራዎችም ከአዲስ አበባ ኤርፖት በተጨማሪ በክልል አየር ማረፊያዎች ለማስተናገድ መታቀዱን ጠቁመዋል።
የክልል ኤርፖርቶችን ማስተሳሰር የቱሪዝም ፍሰቱ እንዲጨምር እንዲሁም የደንበኛውን እንግልት መቀነስ የሚያስችል ነው ያሉት አቶ እንደሻው፤ ለአብነትም ከሚዛን ቴፒ – ጅማ – ጋምቤላ – አሶሳ እንዲሁም ከድሬደዋ – ሃረር – ባሌሮቤ የተሳሰረ በረራ እንዲኖር ለማድረግ መታሰቡን ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም የመንፈሳዊ ጉዞዎችን ከክልል ኤርፖርቶች ለማድረግ እንደሚሰራ ገልጸው የሃጂ ኡምራ ጉዞ፣ ወደ ኢየሩሳሌም፣ ገናን በላሊበላ እና ጥምቀትን በጎንደር ጉዞዎችን ለማስተናገድ ታቅዷል ሲል የዘገበው ኢፕድ ነው።












