በሚቀጥሉት ሁለት ወራት በአዲስ አበባ ይካሄዳሉ ተብሎ የሚጠበቁ ዓለም እና አገር አቀፍ ኮንፈረሶችን አስመልክቶ የከተማ አስተዳደሩ ከሆቴል ኢንዱስትሪ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር የቅድመ ዝግጅት ዉይይት አድርጓል።

የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ላይ ዉይይት መደረጉን ተገለጹት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ “የኮንፍረስ ቱሪዝም ያልተነካ እምቅ ሀብታችን ነዉ” ሲሉ መልእክታቸውን በማህበራዊ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
“የዻጉሜ እና የመስከረም ወራት በመዲናችን አዲስ አበባ ለሚካሄዱት የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ሳምንት፣ ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ፣ ሁለተኛው የካረቢያን እና አፍሪካ መሪዎች “ካሪኮም” ጉባኤን አስመልክቶ ጠቃሚ ውይይት አድረገናል” ነው ያሉት።
አክለውም “የአገራት መሪዎችን ፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የአየር ንብረት ተመራማሪዎችን፣ ዓለም አቀፍ የሚዲያ አካላትን ጨምሮ ከ25 ሺህ በላይ ታዳሚዎች የሚሳተፉበት የአየር ንብረት ጉባኤ በመዲናችን መካሄዱ ባለፉት የለዉጥ ዓመታት ለዘርፉ ልማት የሰጠነዉን ከፍተኛ ትኩረት ተገቢነት የሚያረጋግጡ ማሳያዎች ናቸዉ” ብለዋል።
“መዲናችን አዲስ አበባም ከዚህ ቀደም ከተለመዱ ዉስን ጉባኤዎች በእጥፍ የላቁ ዓለም አቀፍ ኩነቶችን በስኬት በማስተናገድ ላይ ትገኛለች” ያሉት ከንቲባዋ በተያዘው ዓመት የተደረጉ ስኬታማ ጉባኤዎችንም ጠቅሰዋል።
150 ዓለም አቀፍ ኩነቶችን በከፍተኛ ስኬት የተከባወኑ ሲሆን 1.3 ሚሊዮን ያህል ጎብኚዎችንም ያስተናገደችው መዲናዋ፣ በዚህም 143 ቢሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል ነው የተባለው።
የተመዘገበው ከፍተኛ ዉጤት ምክንያት አዲስ የተገነቡና የታደሱ ነባር የቱሪዝም መሰረተ ልማቶች፣ የከተማችን ነዋሪዎች የእንግዳ ተቀባይነትና ተባባሪነት፣ የግሉ ዘርፍ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና የመንግስት የተናበበ ቅንጅት ጉልህ ድርሻ እንደነበራቸው ከንቲባ አዳነች አስታውሰዋል።

የጉባኤዎቹ በአዲስ አበባ መደረግ ለከተማዋ አዲስ ገፅታ፣ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስተዋወቅ ረገድ የሚኖራቸዉ አስተዋፆ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበረው። በመሆኑ ይህንን ግብ ለማሳካት በከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜትና የላቀ የአምባሳደርነት ሚና ይበልጥ ተቀናጅተን መስራታችን እንዲቀጥል ከንቲባዋ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።












