የቢሾፍቱ ዓለምአቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያን መገንባት እያደገ ያለውን የአቪዬሽን ዘርፍ ፍላጎት ለሟሟላት፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሳደግ እና ሀገሪቱ በአቪየሽን ዘርፍ መሪነቷን አጠናክራ እንድትቀጥል ያስችላል ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ።
ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ፤ በ10 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የቢሾፍቱ ዓለምአቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያን ለመንባት እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

ፕሮጀክቱ የአውሮፕላን ማረፊያ ብቻ ሳይሆን፣ የፓና አፍሪካ ትስስርን ለማጠናከር፣ ለኢኮኖሚ ፣ለቱሪዝም እና ለንግድ እድገት እንዲሁም ለባህል ልውውጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።
የአውሮፕላን ማረፊያው የመንገደኞች እና የካርጎ አገልግሎት በመስጠት፤ አብረው መስራት የሚፈልጉ የንግድ አጋሮችንና ዓለም አቀፍ አልሚዎችን መሳብ እንደሚያስችልም ተናግረዋል። አፍሪካን ከዓለም፤ ዓለምን ከአፍሪካ ለማገናኘት፤ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣውን የቱሪዝም ፍሰት በእጥፍ ለማሳደግ እና የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ገንቢ ሚና ያበረክታልም ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
ዘመናዊ የካርጎ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ የሚገነባው የቢሸፍቱ ዓለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፤ ምርቶችን በፍጥነት ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ለማጓጓዝ እንደሚያስችልም ገልጸዋል። የአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ከአራት እጥፍ በላይ በማሳደግ፤ በዓመት ከ110 ሚሊየን በላይ ደንበኞችን ማስናገድ ያስችላልም ነው የተባለው።
ፕሮጀክቱ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች የሥራ እድል ለመፍጠር ከማስቻሉም በላይ፤ በአካባቢውም ሆነ በማኅበረሰብ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማያስከትልም ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ ከሀገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ አጀንዳዎች ጋር የተጣጣመ ነው ያሉት የገንዘብ ሚኒስትሩ፤ የግል ዘርፉን ለማበረታታት፣ የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብና የሀገሪቱን የሎጂስቲክስ አቅም ለማሳደግ ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም አንስተዋል።
ለፕሮጀክቱ ግንባታ ከሚያስፈልገው 10 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ውስጥ የአፍሪካ ልማት ባንክ 80% በመቶ በራሱ እና ብድር በማፈላለግ የሚሸፈን ሲሆን 500 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ባንኩ ፋይናንስ ለማድረግ ትላንት ስምምነት ፈርሟል፤ 20% በመቶ ወጪ በአየር መንገዱ የሚሸፈን ይሆናል።












