ኢራን ከአሜሪካ ጋር ስለሚኖራት የኑክሌር ድርድር ያላትን አቋም በድጋሜ ይፋ አደረገች።
የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ቴህራን በጫና ከአሜሪካ ጋር ወደሚደረግ ድርድር አትመለስም በሚል አረጋግጠዋል። ዋሽንግተን እና የአውሮፓ አገራት በኢራን ላይ አሉታዊ ግፊት ሲያደርጉ የኢራን አቋም እየጠነከረ ይሄዳል ብለዋል።
ኢራን እና የአውሮፓ አገራት በ2015ቱ የኑክሌር ስምምነት ላይ እንዲሁም ቴህራን ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ሀይል ድርጅት ጋር ያላትን ትብብር ስላቋረጠችበት አጋጣሚ ውይይት አድርገዋል። ምንም እንኳን ውይይቱ ቢደረግም ለችግሮች መፍትሄ የሚሆን ስምምነት ላይ ግን አለመድረሳቸው ይታወሳል።
ኢራን ከእስራኤልም ሆነ አሜሪካ በኩል ጥቃት ቢሰነዘርብኝ አጸፋዊ ምላሼ ይከፋል በሚልም ዝታለች። በተለይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰይድ አባስ አራግቺ በጫና የሚሆን ነገር የለም ማለታቸው ውጥረቱን የሚጠቁም አድርጎታል።
ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ንትርክ ውስጥ የገቡት አያቶላዎቹ ወደ ኑክሌር ማበልጸጉ ሂደት መመለሳቸው እንደማይቀር የአሜሪካ ሚዲያዎች እየዘገቡ ነው። አሜሪካ እና ኢራን በኑክሌር ጉዳይ ላይ ካልተስማሙ መላ መካከለኛው ምስራቅ ውጥረት ውስጥ ሊገባ ይችላል ሲል የዘገበው ኒውስዊክ ነው።
በ-ቢኒያም ካሴ












