ሕዝቡ የሚያነሳቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በየደረጃዉ ያሉ አስፈፀሚ አካላት የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረዉ ሊቀጥሉ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገልጸዋል።
በማዕአላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፌዴራል እና የክልል ምክር ቤት የሕዝብ ተወካይ አባላት ከተመረጡባቸዉ አካባቢ ማህበረሰብ ጋር የተወያዩ ሲሆን፤ ከሀዲያ ዞን አስፈፃሚ አካላት ጋር በሆሳዕና ከተማ የጋራ ምክክር መድረክ አካሂደዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የቡድኑ አስተባባሪ አብርሃም አለማየሁ (ዶ/ር) ምክር ቤቱ ለአባላት ከሰጣቸው ተልዕኮዎች መካከል አንዱ የወከለው ህዝብ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙ ማድረግ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፌዴራል እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አባላት በጥምረት በሀዲያ ዞን በሆሳዕና ከተማ አስተዳደርና በሌሞ ወረዳ እየተሠሩ ያሉ የተለያዩ የልማት ሥራዎች ጎብኝተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አነሳሽነት በሌሞ ወረዳ ዱባንቾ ቀበሌ የተጀመረው የገጠር ኮሪደር ልማት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደረገና የአካባቢዉን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለበርካታ የገጠር ወጣቶች ሥራ ዕድል መፍጠር እንደቻለ የምክር ቤት አባላት አረጋግጠዋል።
ይህ የኮሪዶር ልማት የማህበረሰብን የአኗኗር ዘይቤ በማዘመን ከተረጅነት ወደ ምርታማነት በማሸጋገር የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እና የአካባቢውን አግሮ ሥነ ምህዳር በማሻሻል ረገድ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የምክር ቤት አባላት ገልጸዋል።
መረጃው የተወካዮች ምክር ቤት ነው












